አበበ ብርሃኔ

በኪነ-ጥበብ (ዜማ) ዘርፍ የ2010 ዓ.ም. የበጎ ሰው ተሸላሚ

በሀገራችን የሙዚቃ ዜማ ድርሰትን ሥራዬ ብለው የያዙ፣ በርካታ ዜማዎችን ከአንጋፋዎቹ አስከ ወጣቶቹ ድረስ በመድረስ እንዲጫወቱ ያደረጉ፤ የዜማ ደራሲያን ይጠቀሱ ቢባል፤ ከመጀመሪያዎቹ ተራ ስሙ በጉልህ ሊቀመጥ የሚችል የዜማ ደራሲ ነው፤ አበበ ብርሃኔ፡፡

ገና ልጅ እያለ ከታዳጊ ሕፃናት እስከ ከፍተኛ የኪነት ቡድኖች ድረስ የሚቋቋሙበት ወቅት ስለነበር ከትምህርት ሰዓት ውጪ በታዳጊ ኪነት ውስጥ ክራር መጫወት፣ መዝሙር በመድረስና በድምፃዊነት መሳተፍ ጀመረ፡፡ በትምህርት ቤቱ ለሚካሔዱ የተለያዩ መድረኮች መዝሙሮችን በመድረስ ችሎታውም እጅግ ዝነኛ ኾነ፡፡

በ1975 ዓ.ም የ7ተኛ ክፍል ተማሪ እያለ  ጎንደር ከተማ ውስጥ የተቋቋመው ስመ ጥሩው የፋሲለደስ ኪነት ቡድን ውስጥ የመግባት ዕድል ተፈጠረለት፡፡ በዚህ ወቅት ቀለመ ወርቅ ደበበ የሰጡትን የሙዚቃ ዕውቀት እና የተመስጦ ጸጋ ተናግሮ አይጠግበውም፡፡ “እስከዛሬ ድረስ የሠራኋቸው ዜማዎች በቀለመወርቅ ደበበ ሥም ቢወጡ እንኳ ትክክል ነው ብዬ የምቀበል ሰው ነኝ፤ ከእርሳቸው ያገኘሁትን ሥልት እና መላ እየመነዘርኩ ነው የምኖረው፤” ይላል፡፡

በፋሲለደስ የኪነት ቡድን ውስጥ እያለ፤ ይርጋ ዱባለ፣ አሰፉ ደባልቄን የመሳሰሉ ድምጻውያን ነበሩ፡፡ ለአሰፉ ደባልቄ እና ለሰላማዊት ነጋ የዜማ እና የግጥም ድርስቶችን ደርሷል፡፡ በ1978 ዓ.ም. ላይ የፋሲል ኪነት ቡድን በኮሪያ ሶሻሊስት ወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ በመጣበት ጊዜ አበበ ብርሃኔም ከተመረጡት ዘጠኝ ወጣቶች መካከል አንዱ ኾኖ፤ በአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች መድረኮች ላይ ከጎንደር ፋሲለደስ የኪነት ቡድን ጋር ተጫውቷል፡፡ 

ከዚህ በኋላ ወደ ጎንደር የተመለሰ ቢኾንም፤ ብዙም ሳይቆይ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በኮሜዲያን ልመንህ ታደሰ አገናኝነት ከሶል ኩኩ የሙዚቃ ቤት ባለቤት አቶ ሣህሌ ጋር ተዋውቆ የጸጋዬ እሸቱ የ1980 ዓ.ም. የመጀመሪያ አልበም ውስጥ የተካተቱትን “ተከለከለ አሉ”፣ “ያ…ያ..እያለ”፣ “መሸ”፣ “የተካተቱበት አልበም ደርሶ ለድምፃዊው ለቀረፃ ተሰጠ፡፡ በመቀጠል አሰፉ ደባልቄን ከአቶ ሣህሌ ጋር በመመካከር ከጎንደር እንደትመጣ አደረጓት፡፡ “ተው ተው የኔ አከላት” አልበም ላይ ያሉትን ዘፈኖች በሙሉ ድርሰትም የሙዚቃ ቅንብርና ቅጂም አከናውኗል፡፡  በዚሁ ዘመን ውስጥ የተሠሩት የመጀመሪያ ሥራዎች፤ የየሺ እመቤት ዱባለ “ትዝ አለኝ አንድ ሰው”፣ “ናፍቄህ”፣ “ኩራበት”፣ “አወይ ጥሩ ምንጣፍ” የብርቱካን ዱባለ “እርሳኝ ሀሳብ” የተሰኘውን አልበም ሙሉውን ዜማ እና ግጥም፣ የመሳሰሉት ሥራዎች ነበሩ፡፡

ከዚህ በኋላ እንደ ምርት ያመረታቸው የዜማ ሥራዎች በተለያዩ ድምፃውያን ይቀርቡ ጀመር፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ቢኾንም ጥቂቶቹን ለመዘርዘር ያህል፤ ኬኔዲ መንገሻ (“ፋንታዬ”)፣ ጸጋዬ እሸቱ (“ሆዴ ክፉ እዳዬ”፣ “ተጎሳቁላ ሳያት”፣) ቴዎድሮስ ታደሰ (“አጉል ተቆራኝቶኝ”፣ “አሳው ተከማችቶ”) የሺ እመቤት ዱባለ እና ወንድሟ ንጋቱ ዱባለ፣ አበበ ተካ የመጀመሪያ እና ኹለተኛ አልበሙ፣ ተፈራ ነጋሽ ወረታው ውበት እና ገነት ማስረሻ፣ አስናቀ ገብረየስ እና ፍቅረአዲስ ነቅዓ ጥበብ፣ ሀብተ ሚካኤል ደምሴ፣ ማሪቱ ለገሰ፣ የሺመቤት ዱባለ እና ይሁኔ በላይ፣ ማርታ አሻጋሪ፣ ኩኩ ሰብስቤ፣ ውብሸት ፍስሐ፣ ጌታቸው ካሣ (“ቀና ብዬ ሳየው ሰማይ ደፈረሰ”)፣ ነፃነት መለሰ፣ ኂሩት በቀለ፣ ማሕሙድ አሕመድ፣ ብዙነሽ በቀለ እና ጥላሁን ገሠሠ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ማለፊያ ተካ እና አዳነ ተካ፣ ጋሻው አዳል፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ዓለማየሁ እሸቴ (ምሽቱ ደመቀ)፣ ማዲንጎ አፈወርቅ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ አቦነሽ አድነው፣ ፋሲል ደመወዝ፣ ደረጀ ደገፋው፣ በዕውቀቱ ሰው መኾን፣ ተመስገን ታፈሰ፣ ዳዊት ጽጌ (ባላገሩ)፣ ማስተዋል ዕያዩ፣  ከብዙዎቹ መሐል አለፍ አለፍ እያልን የምንጠቅሳቸው ናቸው፡፡

ከእነዚህ ኹሉ ዜማዎች ደራሲው በልዩነት የሚወዳቸው ዜማዎች አሉት፤ እነርሱም፤ የማሕሙድ አሕመድን (“ስንቱን አስታወስኩት”)፣ የኤፍሬም ታምሩን (“ቢልልኝ”)፣ የጸጋዬ እሸቱን (“ሆዴ ክፉ ዕዳዬ”)፣ የብርቱካን ዱባለ (“እርሳኝ ሀሳብ”)፣ ቴዎድሮስ ታደሰ (“አሳው ተከማችቶ”)፣ የፍቅረ አዲስ ነቅዓ ጥበብ (“አንድ ሰው”)፣ ወረታው ውበት (“የኔ ዓለም ሳልጠራ መጣሁ”)፣ የአረጋኸኝ ወራሽ (“ነፋስ ነው ዘመዴ”)፣ የየሺ እመቤት ዱባለ (“ናፍቄህ”) ምርጫዎቹ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ፡- አበበ ብርሃኔ ከ1970ዎቹ አጋማሽ እስከ ዛሬ ከዜማ ድርሰት ያልተነጠለ፣ በቁጥር ከ800 በላይ የዜማ ሥራዎችን ያበረከተ፣ የዜማዎቹ ለዛና የቅኝት ይዘት የተዋጣለት፣ አንዳንድ ሙከራዊ ቅኝቶችን ከገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ትውፊታዊ ዜማዎች በመውሰድ የማዋኀድና አዲስ አድርጎ የማቅረብ ብቃት ያለው ታላቅ የዜማ ደራሲ ነው፡፡ በዛሬው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ያጣነው ራስን ለአንድ ልኅቀት አሳልፎ የመስጠት የዕድሜ ልክ ውሳኔው በሥራዎቹና በሕይወቱ በሚገባ ታይተዋል፡፡