ፀጋዬ ታደሰ

በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ የ2010 ዓ.ም. የበጎ ሰው ተሸላሚ

ፀጋዬ ታደሰ በቀደምት የኢትዮዽያ ዘመናዊ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስም አላቸው፡፡ 1953 . ጀምሮ 10 ዓመታት በእንግሊዝኛው የኢትዮዽያ ሔራልድ ጋዜጣ ሲሰሩ፤ በጥሩ ኤዲተርነታቸው ብቻ ሳይሆን፤ በፓርላማ እና በአፍሪካ ህብረት ዘጋቢነታቸው ነበር የሚታወቁት፡፡ በጋዜጣው ለመጀመሪያ ጊዜ የስፖርት ዓምድን የከፈቱ ናቸው፡፡ብዙ ጀማሪ ጋዜጠኞችን ብዕር እያረቁ ብቁ ያደረጉም እንጂ፡፡

ፀጋዬ በኢትዮዽያ የመጀመሪያው ኢትዮዽያዊ የውጪ ሚዲያ ዘጋቢ (correspondent) ናቸው፡፡ በግዙፉ የእንግሊዝ ዜና አውታር (ሮይተርስ) 37 ዓመት በላይ ሲያገለግሉ፤ በርካታ ችግሮችን እየተጋፈጡ፣ ፈተናዎችን እያለፉ፣ ስኬቶችን እየተጎናፀፉ ነበር፡፡በደፋርነታቸው፣ በፍጥነታቸውና በሙያዊ ስነ ምግባር ጠባቂነታቸው የሚታወቁት ፀጋዬ፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ በደርግና በኢህአዴግ ዘመናት የነበሩ የፖለቲካ ውጥንቅጦችን፣ የህዝብ ንቅናቄዎችን ለዓለሙ ማህበረሰብ ቀድመው አሳውቀዋል፡፡ በዚህም ስማቸውና ስራቸው ከአገራቸው ይልቅ በሌሎች አገሮች ገኖ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡

በክብርና በሽልማት ከሮይተርስ ለጡረታ ወግ እስኪበቁ ድረስ፤ በአዛውንትነት ዘመናቸው ጭምር ከወጣት ጋዜጠኞች ጋር እየተሯሯጡ መረጃ ለማግኘት ያደርጉት በነበረው ትግል በአለቆቻቸው አልፎ በሙያ አጋሮቻቸው ጭምር አድናቆትን እንዲቸሩ አስገድዷል፡፡ በራስ የመተማመን ብቃታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በፍጥነታቸውና ቅልጥፍናቸው አንዳንድ የውጭ ሚዲያ ዘጋቢ ወዳጆቻቸው «የዜና እፍታን ቀድሞ የሚጨልፍ scoop journalist» የሚል ቅፅል ሰጥተዋቸዋል፡፡ጋሽ ፀጋዬ ለበርካታ ዘመናት የኢትዮዽያ ጋዜጠኞች እና በኢትዮዽያ የውጪ ጋዜጠኞች (correspondent) ማህበራትን በሊቀመንበርነት መርተዋል፡፡ አብዛኛው ዘመናቸውን በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ኖሩ እንጂ፤ ስኬታማ መምህርና የግል ማስታወቂያ ድርጅት ባለቤትም ነበሩ፡፡አገራቸውን ይወዳሉ፡፡ ሕዝባቸውን ያከብራሉ፡፡ በሮይተርስ ኤዲቶሪያል ቢገዙም፤ አገራቸውን የሚጎዳ ተግባር አልፈፀሙም፡፡ በዚህም ዛሬ ላይ ፀፀት ውስጥ የሚከታቸው ነገር የለም፡፡ ለቀረባቸው ከአንደበታቸው የሚወጣው አገራዊ ትርክት ያፈዛል፡፡ በሙያቸው ያካበቱትን ዕውቀትና መረጃ ለሌሎች ሲያካፍሉ አይሰስቱም፡፡ ዛሬ ከንቁ አዕምሮና አካላዊ በቃት ጋር እየኖሩ ያሉት 86 ዓመቱ ጎምቱ ጋዜጠኛ ፀጋዬ፤ «ሥራ ይቅደም» በሚል በህዝብ ዘንድ ለመታወቅ ፈቃዳቸው ሳይሆን ቀርቷል፤ እነሆ ቀኑ ፈቅዶ ማንነታቸው ይታወቅ ዘንድ ደረሰ፡፡