አቶ ተቻለ ኃይሌ

በንግድና ስራ ፈጠራ ዘርፍ የ2010 ዓም የበጎ ሰው ተሸላሚ

አቶ ተቻለ ኃይሌ ህዳር 11 ቀን 1933 ዓም በአዲስ አበባ ከተማ ተወልደው ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በቄስ ትምህርት ቤት እና እንዲሁም እስክ 6ኛ ክፍል የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ 13 ዓመት እድሜያቸው ሥራ እንደጀመሩ ፍልውሃ አካባቢ በዘመኑ ካምፖ ግራናቴሪ በሚባል የጣሊያን የከባድ መኪና መጠገኛ ጋራዥ ውስጥ በቀን 0.25 ሣንቲም እየተከፈላቸው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ እራሳቸውን ለማሳደግ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ አብረዋቸው ይሰሩ ከነበሩት ሶስት ወዳጆቻቸው ጋር በንግድ ሽርክና በልደታ ዳርማር ጫማ ፋብሪካ አካባቢ የከባድ መኪና የጥገና ሥራ በሚል ድርጅት ከፍተው ይሰሩ ነበር፡፡

ከዚያም ባላቸው የሥራ ፍቅርና የማደግ ፍላጎት እስከ ዛሬ ድረስ በበቅሎ ቤት አካባቢ በተለምዶ ተቻለ ጋራዥ እየተባለ የሚታወቀውን ጋራዣቸውን በስማቸው ከፍተው የተገለበጡ መኪኖችን መጠገኛ (Body work) የከባድ መኪና ሞተር በማውረድና በመጠገን (mechanical work) በሶስተኛው ክፍል አምቼ ኩባንያ የሚያስመጣቸውን መኪኖች አዳዲስ የነዳጅ መጫኛ ቦቴዎችንና የአዳዲስ መኪና ካሶኒዎችን በመገጣጠም ለረጅም ጊዜ አገልግሎትን ሲሰጡ ቆይተዋል። አሁን ድርጅቱ የሚገኝበትን በቃሊቲ አካባቢ ማስፋፊያ በመጠየቅ በአጠቃላይ የሥራ ዘርፋቸውን ከጥገና ሥራ ወደ ማምረት በመቀየር በትምህርት የተደገፈ ዕውቀት ሳይኖራቸው ይህንን የብረታ ብረት መገጣጠሚያ በአንዱስትሪ መልክ አስፋፍተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የሚታዩትን በበፊት አጠራሩ ሼል አሁን ኦይል ሊቢያ እየተባለ ከሚታወቀው ኩባንያ ጋር እንዲሁም የኖክ ነዳጅ ማደያ ካኖፒዎችን በብዛት የማደያ መጠለያዎችን ሠርተው አስረክበዋል፡፡ እንዲሁም ለአምቼ ኩባንያና ለተለያዩ የስካኒያ አስመጪ ድርጅቶች እጅግ በርካታ የነዳጅ መጫኛ ቦቴዎችን፣ የደረቅ ጭነት ተሽካሚ ካሶኒዎችን፤ በተጨማሪም መሬት ውስጥ ተቀባሪ ታንከሮችን በመስራት አገልግለዋል። አቶ ተቻለ በጊዜው ከነበሩት ባለድርጅቶችም በተለይ የሚጠቀስላቸው የፈጠራ ችሎታቸው ሲሆን በዘመኑ የላሜራ መቁረጫ፤ማጠፊያና መጠቅለያ ባልነበረበት ሰዓት የተቆራረጠ ብረታብረትና ላሜራ በራሳቸው ድርጅት ውስጥ ፈጥረው በመስራት ለማምረቻነት ለብዙ ዓመታት የተገለገሉበት ሲሆን ይህም የማምረቻ መሳርያ በድርጅቱ ውስጥ እንደ ቅርስ ተቀምጦ በዕይታ ላይ ይገኛል።

ባለፉባቸው መንግስታት የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥማቸውም ይህንኑ ተቋቁመው ዘልቀዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ግን ሳይጠቀስ የማይታለፈው 1983 ዓም በቅሎ ቤት አካባቢ የሚገኘው የጦር መሳርያ ግምጃ ቤት ሲፈነዳ የአቶ ተቻለ ኃይሌ ድርጅት ከጎኑ ስለነበር በፍንዳታው ድርጅቱ እንዳለ የወደመና የነበረው እንዳልነበረ የሆነበት ዘመን ሲሆን ፍንዳታው በአገር የደረሰ በመሆኑ ኢንሹራንስም ሆነ ከመንግስት ምንም አይነት ማካካሻ ባለመቀበላቸው ከማግኘት ወደማጣት የተሸጋገሩበት ዘመን ነበር። ነገር ግን አቶ ተቻለንብረቴ ነው እንጂ እውቀቴ አልወደመም” በማለት በቃሊቲ አክባቢ የሚገኘውን አዲሱን ተቻለ ኃይሌ የብረታ ብረት ሥራን መስርተው በትጋት ያጋጠማቸውን ችግር አልፈውታል። ከዚህ ሌላም በመንግስት ድጋፍ የሚያገኙ ተቋማትን በተለያየ መንገድ ተፎካክረው ቢሰሩም፣ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ገበያው ለነዚህ ተቋማት በትዕዛዝ ጭምር ስለሚሰጥ የገጠማቸው ጫና ቀላል ባይሆንም እነዚህ ሁሉ ችግሮች ሳያሸንፋቸው አቅጣጫቸውን በመቀየር ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ በማስመጣት ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳቢዎችንና የተሳቢ መጫኛ ሎቤዶችን በማምረት ለሀገሪቷ አዲስ የሥራ ዘዴ ከመፍጠር ባሻገር ድርጅታቸውንም ወደሚቀጥለው ደረጃ ከፍ አድርገዋል።

ከተለያዩ ተቋማትም ለአገልግሎታቸው የምስክር ወረቀትና ዋንጫዎች ተበርክቶላቸዋል። በበጎ ሥራም ላይ ከተሳተፉባቸው መካከል ወጣት የእግር ኳስ ቡድኖችን በገንዘብና በቁሳቁስ መደገፋቸው ይጠቀሳል። አቶ ተቻለ ከወ/ ላቀች ደበበ ጋር ትዳር መስርተው የሁለት ሴት እና የስድስት ወንድ ልጆች አባት ሲሆኑ አስራ ሶስት የልጅ ልጆችም አፍርተዋል። አቶ ተቻለ 2001 ዓም ባለቤታቸውን በሞት በማጣታቸው ምክንያት ያለጊዜያቸው ራሳቸውን ከሥራ ዓለም አግልለው በጡረታ ላይ ይገኛሉ።