ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ

በሳይንስ ዘርፍ የ2010 ዓ.ም. የበጎ ሰው ተሸላሚ

ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብተው በባዮሎጂ ትምህርት የመጀመርያ ዲግሪ ከያዙ በኋላ፣ ወደ እንግሊዝ በማቅናት ከሜዲሲን ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሊቨርፑል ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀበለዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አባል ሆነው በህክምና ፋኩሊቲ የፓቶሎጂ የትምህርት ክፍል፣ በሜዲካል ፓራሳይቶሎጂም ማስተማር ጀመሩ፡፡ ለተጨማሪ ትምህርትም ወደ ካናዳ ሄደው፣ በወተርሉ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ተከታትለው ሲጨርሱ በዚሁ ዩኒቨርስቲ የላቦራቶሪ አስተማሪ ሆኑ፡፡

ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከተመለሱ በኋላ በባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ተቀጥረው ከማስተማር በተጨማሪ፣ ጨው አልባ ውሃ ውስጥ ስለሚኖሩ አሳዎች ሰፊ ጥናት አደረጉ፡፡ ይህም ጥናታቸውን የኢትዮጵያ ጨው አልባ ውሃዎች (Freshwater Fishes of Ethiopia) በሚል ርዕስ አሰናድተው፣ጥናቱን በስቴንስል አባዝተው ለህትመት ዝግጁ አደረጉት፡፡  በ1965 ዓ.ም የባዮሎጂ ክፍል ኃላፊ ሆነው ከተመረጡ በኋላ፣ ትምህርት ክፍሉ በሰው ሃይል እንዲጠናከር ከማድረግ በተጨማሪ፣ ለጎበዝ ምሩቃን ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ከየክፍለ ሀገሩ ተውጣጥተው በአዳሪ ትምህርት ቤት እንዲመዘገቡ በማድረግ ተመራማሪዎች እንዲበራከቱ አድርገዋል፡፡

የሳይንስ አማካሪ በነበሩበት ጊዜም፣ ነባር እውቀቶች እንዲጠኑ፣ በባህል መድሃኒት ዙርያ ጥናት የሚያደርጉ ግለሰቦች ዩኒቨርስቲው ከበሬታ እንዲሰጣቸውና እውቀታቸው እየዳበረ እንዲመጣ በማገዝ በብዙ ደክመዋል፡፡ የዕጽዋትና የእንስሳት መዘክር እንዲቋቋም ካደረጉ ሳይንቲስቶች መካከልም አንዱ ናቸው፡፡ የድህረ ምረቃ ፕሮግራም ውስጥ በነበሩ ጊዜም፣ መምህራን ለተሻለ ትምህርት ሙሉ ለሙሉ ውጭ ሀገር ሄደው ብቻ ሳይሆን ከእትብታቸው ሳይቆራረጡ የሳንድዊች ፕሮግራም እንዲነደፍ አደርገዋል፡፡ የኢንፎርሜሽን ሳይንስ የትምህርት ክፍል ሲቋቁምም እገዛ አድርገዋል፡፡፡፡

ፕሮፌሰሩ፣ ጼጼ ተብለው ስለሚጠሩና የገንዲ በሽታን ስለሚያስተላልፉ ዝንቦች ትከረት አድርገው ካጠኑዋቸው ጥናቶች መሃል ሲመደብ፣ በአብዮቱ ጊዜ፣ በወሎ ረሃብ ዙርያ፣ ለተከሰተው ችግር መፍትሄ ይሆን ዘንድ፣ ዩፎሮ (UFRRO: UNIVERSITY FAMINE RELIEF AND REHABILITATION ORGANANIZATRION) የተሰኘ ድርጅት ከመሰሎቻቸው ጋር አቋቁመው፣ ለሁለት ሳምንታት ድርቁ በተከሰተባቸው ቦታዎች በመዘዋወር ያለውን ሁኔታ አጥንተዋል፡፡ በእድገት በህብረት ዘመቻ ወቅትም የዘመቻው ተሳታፊ ሆነው፣ ወደከረን አምርተው ነበር፡፡

ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት ያገለገሉት ፕሮፌሰር ሽብሩ በ1985 ዓ.ም ከዩኒቨርስቲ ከተባረሩት 42 መምህራን መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ከ1986 ጀምሮ በግል ስራ የተሰማሩት እኝህ ምሁር፣ ወደ ታንዛንያና ዛምቢያ በመመላለስ፣ በሁለቱ ሀገራት ባሉ ዩኒቨርስቲዎች አስተምረዋል፡፡ ኢኮ ኮንሳልት ፒ ኤል ሲ የአማካሪ ድርጅት አቋቁመውም በሃላፊነት ሰርተዋል፡፡ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ በተባበሩት መንግስታት የልማት ተቋምና በዓለም ባንክ የማማከር አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ በበጎ ፍቃደኝነትም መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ አገልግለዋል፡፡ጥቂቶቹን ለመዘርዘር ያህልም፣ በአይ ዲ ኢ እና ከኢትዮጵያ ረሃብን ለማስወገድ በተቋቋመ ድርጅት ውስጥ፣ በኢትዮጵያ የዱር እንስሳትና የተፈጥሮ ሀብት ታሪክ ማህበር ውስጥ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ማህበር ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት እና የተፈጥሮ ማህበር ውስጥ በሚሰሩበት ጊዜ ከወዳጆቻቸው ጋር በመሆን ያሳተሙት ዋናና ልዩ ልዩ የሆኑ የአዕዋፍ መኖርያ አካባቢዎች የተሰኘ መጽሐፋቸው Bird life interenaitonal የተሰኘው ድርጅት አፍሪቃ ውስጥ ከታተሙ ይህን መሰል መጻሕፍት መካከል እንደ ጥሩ ምሳሌ አንስቶታል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ሳሉ፣ በተለያዩ አገልግሎቶች የሚታወቁ ሲሆን፣ የባይሎጂ ዲፓርትመንት ሃላፊ፣ የጥናትና ምርምር ህትመት ተባባሪ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የስኩል ኦፍ ግራጁዌት ስተዲስ ዲንና የፓዝ ኦብዮሎጂ ዳይሬክተር በመሆን፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቦርድ አባል ሆነው ሠርተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አባል ናቸው፡፡ አካዳሚውንም በስራ አሰፈጻሚ ዳይሬክተርነት መርተውታል፡፡ ከማስተማር፣ ከማማከርና ከምርምር ሥራዎቻቸው ውጪ፣ የህይወት ታሪካቸውን፣ ‹ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ›፣ በሚል ርዕስ ጽፈው ያስነበቡ ሲሆን በቅርቡ ‹ሕያው ፈለግ› በሚል ርእስ አንድ ሳይንሳዊ መጽሐፍና የስንኝ ማሰሮ በተሰኘ የግጥም መጽሐፋቸው በአንባብያን ይታወቃሉ፡፡