አባ ገብረ መስቀል ተሰማ

በቅርስና ባህል ዘርፍ የ2010 ዓ.ም. የበጎ ሰው ተሸላሚ

አባ ገብረ መስቀል በሰሜን ወሎ ዞን፣ ዋድላ ወረዳ፣ ከግሼና ከተማ አጠግብ አራት ውቅር አብያተ ክርስቲያንትን የሠሩ አባት ናቸው፡፡

ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍለው የተሠሩት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን፣ በኢትዮጵያም ኾነ በዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ዘንድ በታሪካዊነታቸው ጎልተው ይታወቃሉ፡፡ አብያተ ክርስቲያኑ፣ በጠቢባን እጆች የተሠሩት ወይም የተፈለፈሉት፣ 12ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት በተመለከተ ማን ነው የሠራቸው? በሚለው ላይ ለዘመናት የቆየ ክርክር አለ፡፡የጥበቡ ባለቤት ሌላ ነው፤ ከሀገሪቱም ውጭ ነው፤ወደ ማለት ያመሩ አሉ፤የሚሠሩም ከኾነ እስኪ ይድገሙት፤ያሉም አልጠፉም፡፡

አባ ገብረ መስቀል ተሰማ ዐዲስ ሕንፃ አብያተ ክርስቲያን ከወጥ ዐለት በመፈልፈል ለዚህ ለዘመናት የቆየ ጥያቄ ተግባራዊ መልስ ሰጥተዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያኑን ፈልፍለው ለመጨረስ አራት ዓመት ፈጅቶባቸውል፡፡ ሥነ ሕንፃውም፣ እርሳቸው ምን ያህል በጥበብ የተሞሉ መኾናቸውን ያሳያል፡፡ የአርክቴክቸርም ሆነ የምሕንድስና ትምህርት ሳይኖራቸው የሠሯቸው ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የጥንቱ ጥበብ ዛሬም ከኢትዮጵያውያን እንዳልተለየ ማሳያ ናቸው፡፡

ቢቢሲ በዩኔስኮ የተመዘገቡ የቅርስ ሥፍራዎችና የብዙኃን ጎብኚዎች መዳረሻ የኾኑት ኢትዮጵያውያን፣ 800 ዓመት በፊት የሠሩትን ታሪክ በራሳቸው እጅ ደግመውታል፤ የሚል ሐሳብ ያለውን ዘገባ በቅርቡ አውጥቷል፡፡

‹ዳግማዊ ላሊበላ› የሚል ስያሜ የተሰጣቸው አብያተ ክርስቲያኑ፣ በሰሜን ወሎ ዞን ዋድላ ወረዳ ከጋሸና ከተማ በስተሰሜን አቅጣጫ ለላሊበላ ከተማ ቀረብ ባለ ሥፍራ ነው እየታነፁ ያሉት፡፡ ቢቢሲ ታዲያ፣በጥልቀትም ኾነ በጥበብ መገለጫ የሌላቸው ላሊበላን የመሰሉ ውቅር አብያተ ክርስቲያን በኢትዮጵያውያን እየተደገሙ ነው፤ የሚል መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡

‹ጥበቡ የፈጣሪ ነው፤ እኔ የእርሱ መሣሪያ ነኝ› የሚሉት አባ ገብረ መስቀል ተሰማ፣ ቤተ መቅደሱን በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ፈቃዱ ከእግዚአብሔር ነው፤ ሃይማኖታዊና አገራዊ ፋይዳ አለው፤ እንደ ሃይማኖታዊነቱ፣ ጥንቱንም የቅዱስ ላሊበላ ቦታ ነው፤ ከግራኝ አሕመድ ጋር ተደር በነበረው ጦርነት ጊዜ ላዩ ጠፍቶ ስለነበር እርሱን ለመመለስ ነው፤በማለት ያስረዳሉ፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጡ ጎብኚዎች 90 በመቶዎቹ ፍላጎታቸው ላሊበላን መጎብኘት ነው፡፡ በአቅራቢያው ሌላ ከአለት የተወቀረና የተፈለፈለ ጥበብ መፈጠሩ፣ ሌላ ዕድል ሌላ ገቢ ይዞ እንደሚመጣ፣ ተጨማሪ በርካታ ቱሪስቶችንም እንደሚስብ ይጠበቃል፡፡

አባ ገብረ መስቀል ሌሎችንም በማነፅ ላይ ናቸው፡፡ በሥራቸው ግን፣ ዘመናዊ መሣሪያን አይጠቀሙም፡፡