አቶ መኮንን ሙላት

በበጎ አድራጎት ዘርፍ የ2010 ዓ.ም. የበጎ ሰው ተሸላሚ

አቶ መኮንን ሙላት ከባለቤታቸዉ ወ/ሮ ሚርያ ሂማነን ጋር በመሆን ከ30 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ መስማት ለተሳናቸው ወገኖቻችን የተዘጉ በሮችን በመክፈት ፈር ቀዳጅ የሆኑ በርካታ ሥራዎችን አበርክተዋል፡፡ ዋና ዋናዎቹ ተግባሮቻቸዉ እና ያመጧቸዉ ለዉጦች፡ በአካል ጉዳታቸዉ ምክንያት በድህነት ያሉ እና የማህበራዊ ግልጋሎቶችን በቀላሉ ማግኘት ላልቻሉት  መስማት ለተሳናቸዉ ህጻናት እና የህብረተሰቡ ክፍሎች የትምህርት አቅርቦትን በማሻሻል ያደረጉት አስተዋፅኦ በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡

በሆሳዕና ት/ቤት ዉስጥ አቶ መኮንን እና ባለቤታቸዉ ጥራት ያለው ትምህርት በመሥጠት ምስጉን መምህራን ነበሩ፡፡ ሆሳዕና አዳሪ መስማት የተሳናቸው ት/ቤት ተጨማሪ ተማሪዎችን የመቀበል አቅሙ ከፍ እንዲል በዕውቀትና በፋይናንስ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ ከነበረበት የአንደኛ ደረጃ የትምርህት አቅርቦት ወደ ሁለተኛ ደረጃ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና ተጫዉተዋል፡፡ ትምህርት ቤቱን ልዩ የሚያደረገው የሙያ ትምህርት እንዲስፋፋ ከፊንላንድ አገር ባለሙያ በማስመጣት ከሌሎች ትምህርት ቤቶች በተለየ መልኩ በትምህርት ቤቱ የሙያ ትምህርት እንዲስፋፋ እንዲሁም ከትምህርት ቤቱ ሲጨርሱ/  የሚወጡት ጊዜ መስማት የተሳናቸዉ ወጣቶች የሙያ ባለቤት እና ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡

በሀገሪቷ የልዩ ፍላጎት ባለሙያዎች ቁጥርና ብቃት እንዲጨምር፡ የትምህርት  ቤቱ መምህራን አቅም በየጊዜዉ  እንዲጎለብት እና ሙያቸዉን የበለጠ እንዲወዱት እንዲያስችል  በአገር ውስጥና ከሀገር ውጪ (በፊንላንድ) ትምህርት እድል እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ መስማት ለተሳናቸው የሚሰጠው አገልግሎት ነፃ ከመሆኑ አንጻር የበጎ አድራት እጅ መጠበቁ የግድ ነበር፤ ለዚህ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የገንዘብ ምንጭ እዲገኝ ግንባር ቀደም ድርሻ አላቸው፡፡

ትምህርት ቤቱ የሌሎችን እጅ ጠባቂ ብቻ እንዳይሆን የራሱንም የውስጥ ገቢ እንዲያዳብር፣ እንጨት ሥራ፣ ብረታብረት፣ እርሻ፣ ከብት ማድለብ፣ ወዘተ. ሥራ እንዲሠራ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ከትምህርት ቤቱ ውጪ በርካታ የልዩ ፍላጎት መምህራንን አቅም አጎልብተዋል፤ ለበርካታ መደበኛ መምህራን የምልክት ቋንቋና መስማት የተሳናቸውን የማስተማር ሥነ ዘዴ ስልጠና በመስጠት የአካቶ ትምህርት በተሻለ እንዲተገበር አድርገዋል፡፡ በብዙ ት/ቤቶች ውስጥ መስማት ለተሳናቸው ልዩ ክፍሎች እንዲከፈቱ በማድረግ ከትምህርት ቤት ጀምሮ በትምህርት አስተዳደር ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ተከታታይ የግንዛቤ ማዳበርያ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡

ቀድሞ ምንም ያልነበሩትን መስማት ለተሳናቸዉ ተማሪዎች የሚመጥኑ የመማር ማስተማሪያ  መጽሀፍትና ቁሳቁስ በማዘጋጀት ለበርካታ ት/ቤቶች አሰራጨተዋል፡፡ በወረዳ ከተሞችና በየገጠሩ ተረስተው የትምህርት እድል ያጡ መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች ከተደበቁበት ወጥተው የትምህርት እድል እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡ የወረዳ ት/ቢሮዎች የሰው ኃይል (መምህር) ሲያጥራቸው ለጊዜው በመቅጠር የትምህርት ሥራው እንዳይስተጓጎል አድርገዋል፡፡ በአንዳንድ ት/ቤቶች የመማሪያ ክፍሎችና አካባቢዎች ምቹ እንዲሆኑ አድርገዋል (ለምሳሌ ለመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ወይም ጥገና ማድረግና ሽንት ቤቶችን ማሰራት)፡፡ በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ መስማት የተሳናቸውን በማደራጀት ሥራ እንዲፈጥሩ የማቴርያል፤ የገንዘብና ሥነልቦናዊ ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡

ባለፉት 10 አመታት በሀገሪቱ ለሚገኙት መስማት የተሳናቸዉ ሰዎች ኑሮ መለወጥ የአቶ መኮንን እና የባለቤታቸዉ አስተዋፅኦና ጥረት የአንበሳዉን ድርሻ ይይዛል፡፡ እስካሁን  በአስር ሺህ የሚቆጠሩ መስማት የተሳናቸዉ ህፃናትና ወጣቶች መብታቸዉ የሆነዉን የትምህርት እድልና የተለያዩ ክህሎቶች እንዲያገኙ አመቻችተዋል፡፡ የዛሬ አስር አመት አንድም መስማት የተሳነው ተማሪ ዩኒቨርሲቲ መግባት የማይችልበት ግዜ ሲሆን ዛሬ በተለያየ የትምህርት ክፍሎች በመጀመርያ ድግሪ የሚማሩ ከ70 በላይ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ገብተው በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡ በማስተርስ ደግሪም ደረጃ በመማርና ላይ ያሉና የተመረቁም ብዙ አሉ፡፡

አቶ መኮንንን እና ባለቤታቸዉን እጅግ ለየት የሚያደርጋቸዉ የተከሉትን ችግኝ እስከመጨረሻዉ መንከባከባቸዉ ነዉ፡፡ በተማሪዎቻቸዉ እና በሚሰሩት ስራ ላይ ልዩ ክትትልና የእርምት እርምጃ በመውሰድ፡ የገንዘብ ችግር ያላቸዉን ተማሪዎች ከኪሳቸዉ አግዘዉ ጠንካራ ሥራ ተሠርቶ ውጤት ያለው ፍሬ እንዲያፈራ አድርገዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ተግባሮቻው በአገሪቱ ያሉትን የልዩ ፍላጎት ባለሙያዎች እና ጉዳዩ ያገባኛል የሚሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች  በማስተባበርና አብሮ በመስራት ወደር የማይገኝለት ተግባር ፈጽመዋል፡፡

ያገኙትን የገንዘብ ድጋፍ በአብዛኛው እነሱ መሥራት የሚችሉትን ራሳቸው በመሥራት (ለምሳሌ፣ የመጽሐፍና የትምህርት መርጃ መሣርዎች ዝግጂቶችን በማዘጋጀት)፣ ሀብትን በመቆጠብና ላሰቡለት ዓላማ ብቻ እንዲዉል በማድረግ የሚገርም ተግባር ፈጽመዋል፡፡