ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም

መንግስታዊ ሃላፊነትን በብቃት በመወጣት ዘርፍ የ2010 ዓ.ም. የበጎ ሰው ተሸላሚ

ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም የመንግሥት ኃላፊነትን የጀመሩት ገና በሰባት ዓመታቸው ደጃዝማች ተብለው በሞግዚት አስተዳደር የተንቤን አስተዳዳሪ በመሆን ነው፡፡ ከዚህ ሹመት በኋላ በጠላት ወረራ ዘመን በአስመራ እና በሮም በግዞት ለአራት ዓመታት ቆይተዋል፡፡ ጠላት ጣልያን ከሀገር ከተባረረም በኋላም በቀዳማዊ ወያኔ እንቅስቃሴ መሪነት ተጠርጥረው በምርመራና በቁም እስር ለሰባት ወራት በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ቆይተዋል፡፡

ልዑል ራስ መንገሻ ከተንቤን በመቀጠል በሸዋ ጠቅላይ ግዛት የጅባትና ሜጫ አውራጃ ገዢ ሆነው ተሹመው ለአካባቢው የኤሌክትሪክ መስመር በመዘርጋት፣ ድልድዮችን በመገንባት፣ የሕክምና ተቋማትን በማስፋፋትና የግብርና ልማት ጣቢያዎችን በማስጀመር ውጤታማ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ከዚያም ወደ አርሲ ጠቅላይ ግዛት ገዢነት ተዛውረው አገልግለዋል፡፡ በዚሁ ወቅት ጢቾንና አሰላን የሚያገናኝ ጥርጊያ መንገድ፣ ከአሰላ እስከ ዝዋይ መንገድ አሠርተዋል፡፡ በግብርናው ዘርፍም ከጣልያኖች ልምድ በመውሰድ ዘመናዊ የበግ እርባትን እንዲሁም ከስውድኖች ተሞክሮ ዘመናዊ የስንዴ ልማትን ለአካባቢው አርሶ አደሮች አስተዋውቀዋል፡፡

ልዑል ራስ መንገሻ በ1948 ዓ.ም ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት አገረ ገዢነት ተሸመው  የይርጋ ጨፌ ቡና በዓለም አቀፍ የቡና ገበያ እንዲታወቅና በወቅቱ የተሻለ ገቢ እንዲያስገኝ ከእርሻ ሚኒስቴር ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ጋር በመሆን አመርቂ ሥራ ሠርተዋል፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከኬኒያ ጋር የምትዋሰንበት የቦረና ድንበር የአጼ ምኒልክን ዘመን የድንበር ሁኔታ ያላከበረ በመሆኑ ከአካባቢው ማኅበረሰብ በመረዳት ጉዳዩን እስከ ንጉሠ ነገሥቱ ድረስ አድርሰው በማስረዳት ድንበሩ ወደ ጥንት ይዞታው እንዲመለስ አድርገዋል፡፡ ለአካባቢው አርብቶ አደሮች የሚሆኑ የውሃ ግድቦችንም አሠረተዋል፡፡ በ1949 ዓ.ም ተቆርቁራ የጠቅላይ ግዛቱ ርዕሰ ከተማ እንድትሆን በ1953 ዓ.ም የተፈቀደላትን የዛሬዋን ሐዋሳ የመሠረቷት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ናቸው፡፡

ከሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ወደ ሥራና መገናኛ ሚኒስቴር ተዛውረው ተቋሙን በሚኒስትርነት መርተዋል፡፡ በዚህም ወቅት ከጎሃ ጽዮን በአባይ ሸለቆ እስከ ደብረ ማርቆስ ያለውን መንገድ ከጠላት ወረራ በኋላ ባማረ ሁኔታ እንዲጠገን አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም የሐዋሳ፣ መቀሌና ባሕዳር ከተሞች ፕላን በዘመናዊ መንገድ እንዲሠራ አድርገዋል፡፡ ልዑል ራስ መንገሻ የሥራና መገናኛ ሚኒስቴርን ሲመሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለጄት ሞተር ዘመናዊ አውሮፕላኖች እንዲኖሩት የሚኒስሮች ምክር ቤትን፣ ጃንሆይንና አበዳሪ ተቋማት በማሳመን ታሪካዊ ሥራ አከናውነዋል፡፡ የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያም የመጀመሪያው ምዕራፍ የተሰራው በእሳቸው የሚኒስርነት ዘመን ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሕንጻ በአዲስ አበባ ሲገነባ የሕንጻው ሥራ በቀን በሦስት ፈረቃ በአንድ ዓመት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በኢትዮ - ጂቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ውስጥ የጎላ ድርሻ እንዲኖራቸውም አድርገዋል፡፡

ልዑል ራስ መንገሻ የ1953 ዓ.ም መንፈቅለ መንግሥትን ተከትሎ አባታቸው በማረፋቸው ምክንያት የትግራይ ጠቅላይ ግዛት አገረ ገዢ ሆነው ተሹመዋል፡፡ በትግራይ የመጀመሪያ ሥራቸው አስቸጋሪውን መልክዐምድር በመቋቋም የመንገድ መሠረት ልማትን ማስፋፋት ነበር፡፡ በዚህም በመሶበ፣ በዳሎል፣ በአሌቲና መንገዶች የተሳካ ተግባር አከናውነዋል፡፡ በሌላም በኩል የትግራይ ልማት ድርጅት የተሰኘ ተቋም በማቋቋም የአካባቢውን ሕዝብ ችግር መንስዔዎችን እያስጠኑ የሚቀርቡትን የመፍትሔ እርምጃዎች በመተግበር ውጤታማ ሥራ አከናውነዋል፡፡

ለአካባቢው ልማት የሚያስፈልገውን የሰው ጉልበትና ለእርዳታ የሚመጣውን እህል በማጣመር ምግብ ለሥራ የተሰኘ መርሀ ግብር ቀርጸው ሰፋ ያለ የእርከን ሥራ አከናውነዋል፡፡ ልዑል ራስ መንገሻ በእነዚህ ሁሉ ሥራ አሠሪ ብቻ ሳይሆኑ በቀጥታ በሥራው ተሳታፊም ነበሩ፡፡ የመንገድ ሥራ ሲሰራ ንድፍ ከማውጣት ዶዘር እስከማሽከርከር፣ የስፖርት ባሕልን ለማዳብር ትጥቅ ለብሶ በጨዋታ ሜዳ እስከመሳተፍ የደረሰ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ የትግራይ አገረ ገዢ በነበሩበት ወቅት የመቀሌ ከተማ የተሻለ ፕላን እንድታገኝና በርካታ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች እንዲኖራት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡

ልዑል ራስ መንገሻ የ1966 ዓ.ም አብዮት ተከትሎ ለስደት ተዳርገው ለብዙ ዓመታት በውጭ ሀገራት ኖረዋል፡፡ የደርግን መውደቅ ተከትሎም ወደ ሀገራቸው በመመለስ በበርካታ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ ናቸው፡፡