ሬልዶፍ ኬ. ሞልቬር - Reidulf K. Molvaer

ለኢትዮጵያ በጎ የሰሩ የውጪ ሃገር ሰዎች ዘርፍ የ2010 ዓም የበጎ ሰው ተሸላሚ

ሩዶልፍ ሞልቬር የኖርዌይ ዜግነት ያላቸው ተመራማሪ ሲሆኑ ለ14 ዓመታት በኢትዮጵያ ኖረዋል፡፡ በኢትዮጵያ በኖሩበት ጊዜም፣ የሀገሪቱን የሥነጽሑፍ ደረጃ ወደፊትና ወደኋላ በመሄድ አጥንተዋል፤ ባህላዊ መድኃኒቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ስላላቸው ደረጃ ጠቁመዋል፡፡

ሞልቬር የተለያዩ መጻሕፍትን በኢትዮጵያ ሥነ ቋንቋ፣ ታሪክና ማህበራዊ ሁነቶች ላይ ተመስርተው ጽፈው አስነብበዋል፡፡

Tradition and change in Ethiopia፣ Socialization and social control in Ethiopia Black Lions: the creative lines of Ethiopia’s Literary Giants and pioneers የተሰኙ መጻሕፍትን በማዘጋጀትና Prowess, piety, and politics: The chronicle of Abetto Iyassu and Empress Zewdittu የተባለውን ነባር መጽሐፍ አርትኦት በማድረግ ስለ ሀገራችን ሁኔታ ለማሳየትና ለማስተዋወቅ ሞክረዋል፡፡

ሞልቬር በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍና ደራስያን ታሪክ ላይ የሚሰሩዋቸው ጥናታዊ ጽሑፎች፣ በየጊዜው እንደ መረጃ ምንጭነት የሚጠቀስና ስለኢትዮጵያ ደራስያን ህይወትና ትኩረት ዓለም እንዲያውቀው ካደረጉ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡

እስካሁንም ድረስ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተመራማሪዎች ዘንድ በእሳቸው ደረጃ የበርካታ ደራስያንን ህይወትን የመረመረና ሥራዎቻቸው ምን ላይ እንደሚያተኩሩ የፈተሸ ምሁር እንደሌለም ይነገራል፡፡ መዝገበ ቃላት በማዘጋጀት የሚታወቁትን የእነአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ድካም አንስቶ እስከ በዓሉ ግርማ በድርሰቱ ሰበብ ስለከፈለው መስዋእትነት የሚተርከው Black Lions የተሰኘው ደጎስ ያለ መጽሐፋቸው ብዙኃኑ ዘንድ የሚጠቀስላቸው ሲሆን፣ እሱን መሰል ስራም፣ ከእሳቸው በፊትም ሆነ በኋላ በሌሎች ሰዎች ዘንድ እንዳልተሰራ ይነገራል፡፡

ሞልቬር በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሉተራን ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት፣ የኢቫንጀሊካል ኮሌጅ መምህር፣ የወንጌል ራዲዮ አርታዒ በመሆን አገልግለዋል፡፡