አቶ ዳዊት ኃይሉ

በበጎ አድራጎት ዘርፍ የ2009 የበጎ ሰው ተሸላሚ

አቶ ዳዊት ኃይሉ በዐርባዎቹ መጀመሪያ የሚገኙ የውዳሴ ዳያግኖስቲክ ማዕከል ባለቤት ናቸው፡፡ ውዳሴ ዳያግኖስቲክ የአልትራ ሳውንድ፣ ኤም አር አይ እና ሲቲ ስካንን የመሳሰሉ ጨረር፣ ማግኔትና ድምጽ በመጠቀም በአካል ውስጥ ያሉ በሽታና ችግር ለመለየት የሚጠቅሙ መሣሪያዎችን በማስመጣት ሕዝብ ከሚያገለግሉ ተቋማት አንዱ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሲቲ ስካን ከ1150 ብር እስከ 3000 ብር፣ ኤም አር አይ ደግሞ ከ2000 እስከ 3000 ብር ያስከፍላል፡፡ የአቶ ዳዊት ማዕከል የመክፈል ዐቅም ለሌላቸው ነገር ግን ከፍተኛ የጤና ችግር ላለባቸው ችግረኞች የተለየ አሠራር ይከተላል፡፡ ተቋሙ ከተመሠረተበት ከ2001 ዓም ጀምሮ በአማካኝ በቀን ከ10 እስከ 18 ለሚደርሱ ችግረኞች የነጻ ምርመራውን ያከናውናል፡፤ ከዚህም በተጨማሪ በየዓመቱ በጳጉሜ ወር በየቀኑ ከ40 እስከ 50 ለሚደርሱ ችግረኛ ሕሙማን የነጻ አገልግሎት ይሰጣል፡፤ ይህንን ለማድረግም በሽተኞቹን የገንዘብ ዐቅማቸው የሚገልጥ የተለየ ደብዳቤ አይጠይቅም፡፡ የማዕከሉ ባለሞያዎችና ችግረኞቹን በቀጥታ የሚያገኟቸው የሕክምና ባለሞያዎች የሚሰጡት መግለጫ በቂያቸው ነው፡፡ በችግረኛ ሰው ላይ ከሚታየው የአካልና የስሜት ጉስቁልና ራሱን የሚገልጥለት የለም ይላሉ፡፡

አንዳንዴም ችግራቸው በልብስ የሸፈኑ፣ ሲያዩዋቸው መልካም ኑሮ ያላቸው ሰዎች ይመጣሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ችግራቸውን ሰምቶ የሚይዝላቸው፣ ግን ደግሞ የሚረዳቸው ባለሞያ ይፈልጋሉ፡፡ የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ባለሞያዎች እነዚህን ሰዎች እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው ትምህርትና መመሪያ አላቸው፡፡ ይህም የአቶ ዳዊት መርሕ ውጤት ነው፡፡

በድርጅታቸው አገልግሎት ፍለጋ ከሚመጡ ሕሙማን መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት በሽታቸው በአግባቡ የመለየት ዕድል ስላለው ተገቢውን ሕክምና ካገኙ የመዳን ዕድል አላቸው፡፡ ይህን የሚረዱት ተገልጋዮች ዐቅማቸው በደከመበት ጊዜ በነጻ አገልግሎት ቢያገኙም ዐቅም ሲኖራቸው ግን ለመክፈል ተመልሰው ይመጣሉ፡፡ እስከዛሬም ድረስ ከ24800 ለሚበልጡ ችግረኞች ነጻ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡

 

በእነዚህና በሌሎች ለሀገራቸው በሠሯቸው ሥራዎች ምክንያት በዳኞች ውሳኔ በ2009 ዓም በበጎ አድራጎት ዘርፍ የዓመቱ በጎ ሰው ተሸላሚ ሆነዋል፡፡