ንጉሤ አክሊሉ

በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ የ2009 የበጎ ሰው ተሸላሚ

ንጉሤ አክሊሉ በ1941 ዓ.ም ሰኔ 18 ቀን 4 ኪሎ በኣታ ለማርያም ገዳም አካባቢ ተወለደ፡፡ አባቱ አፈ ሊቅ አክሊሉ ሲባሉ እናቱ ወ/ሮ የሺ ገብረ ኪሮስ ይባላሉ፡፡ የመጀመሪያ ትምህርቱን በመንፈሳዊ ትምህርት የጀመረው ንጉሤ ፊደል የቆጠረው፣ ዳዊት የደገመው፣ ወንጌል ያነበበው በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ የመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ ት/ቤት ነው፡፡

ከንባቡ ትምህርት በኋላ ዜማ ቤት ገብቶ ድጓውን፣ ጾመ ድጓውን በሚገባ ተምሮ አስመስክሯል፡፡  ዜማውን ከሁለት መምህራን ተምሮታል፡፡ በተጨማሪም ቅዳሴ፣ ቅኔና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በሚገባ ተምሯል፡፡ በተጓዳኝም በዚሁ ትምህርት ቤት ይስጥ የነበረውን ዘመናዊ ትምህርት በመከታተል የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታተለ፡፡

በ1965 ዓ.ም አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ጨርሶ ወደ ኮከበ ጽባሕ ከመሔዱ በፊት በዲፕሎማ ከዛው ከዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ የመምህራንና ቀሳውስት ማሰልጠኛ ተቋም ተመርቋል፡፡ በወቅቱ ተገኝተው ተማሪዎቹን የመረቁት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ነበሩ፡፡ 

የንጉሤ አባት ጋዜጠኛ ነበሩ፡፡ በቤተ ክህነት ታሪክ ከመጀመሪያዎቹ የጋዜጦች አዘጋጆች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በተለይም በዋናነት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን መጽሔት ዜና ባስልዮስ፣ ዜና ተክለ ሃይማኖትንና ዜና ቤተ ክርስቲያንም ያዘጋጁ ነበር፡፡ በዚህም የንጉሤ የጋዜጠኝነት ዝንባሌው እየጨመረ መጣ፡፡

አፈሊቅ አክሊሉ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ሲሠሩ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያመጡ ነበር፡፡ ለዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ የቀሳውስት ማሠልጠኛ ት/ቤት ላሉ መጽሕፍት ሊቃውንት መምህሩ ለሊቀ ሊቃውንት ሞገስ ወ/ማርያም፣ ለንጉሤ የቅኔ መምህር ለመጋቤ ምሥጢር ጌራ ወርቅ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያመጡላቸው ነበር፡፡ ንጉሤም እርሳቸው የሚያመጡትን ጋዜጣ እያነበበ የዕውቀት አድማሱን አስፋፋ፡፡ በተለይም ከ1958 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ልዩ ልዩ ጽሑፎችን ማቅረብ ጀመረ፡፡ እንግዲህ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 50 ዓመታት በዚህ በሥነ ጽሑፍ ሥራ ቆይቷል ማለት ነው፡፡ 

ወደ ኮከበ ጽባሕ ከመሔዱ በፊት የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለ የትምህርት ቤቱ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ የስፖርት ዜና፣ ሌሎችም የቤተ ክርስቲያን በዓላት ዜና ለተማሪዎች ሰንደቅ ዓላማ ከተሰቀለ በኋላ በየዕለቱና በየሳምንቱ ያቀርብ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መንፈሳዊም ሥጋዊም ቲያትሮችን እየደረሰ ከጓደኞቹ ጋር ያቀርብ ነበር፡፡

ወደፊት ደመወዝ ይከፈልሃል በሚል ኮከበ ጽባሕ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እየተከታተለ እዛ የሚተላለፉትን ትምህርቶች ከሊቃውንት እወሰደ ለሚዲያ በሚያመች ሁኔታ እያዘጋጀ ያቀርብ ነበር፡፡

የጋዜጠኝነት ሙያ ከተከታተለ በኋላ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የዜና ተቀባዮች ፈተና ተፈትኖ አልፎ ተቀጠረ፡፡ በዚያም ሥራው ከክፍለ ሀገር የሚመጡትን ዜናዎች መቀበል ነበር፡፡ ቀጥሎም በሪፖርተርነት መሥራት ጀመረ፡፡ በአጭር ጊዜ በሥራውም ውጤታማ ሆነ፡፡ በዚህም ለአምስት ዓመት ከሠራ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ተዛወረ፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እየሠራም የጋዜጠኝነት ኮርስ በውጭም በውስጥም ተከታትሎ ሙያውን አሻሽሎ ውጤታማ ሥራ ሊሠራ ቻለ፡፡ 

ንጉሤ በሬዲዮ ለብዙ ዓመታት ሠርቷል፡፡ በተለይ በሕዝብ ዘንድ በታወቀው የእሑድ ጠዋት ፕሮግራም ከ1973-1977 ዓ.ም ድረስ ሠርቷል፡፡ ከእሑድ ፕሮግራም በተጨማሪ ከከተማ ማኅበራትየሚል በርካታ ሕዝብ የሚያዳምጠውን ፕሮግራም አዘጋጅቶ ያቀርብ ነበር፡፡ በሚያቀርባቸው ልዩ ዝግጅቶች ሕዝባዊ ወገናዊነቱን ያሣየ በሕዝብ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነትን በማግኘቱ ከደርግም ጋር ሲተም የኖረ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በራጉኤል ቤተ ክርስቲያን በተነሣው ክርክርና የሰፈራ ፕሮግራምን ድክመት አጋለጥክ በሚል ምክንያት ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ተሰናበተ፡፡

ከዚያም የሚወደውንና ያደገበትን የሬዲዮ ሥራ ትቶ ወደ ብሔራዊ ሎተሪ ተዛወሮ የማስታወቂያ ክፍል ኃላፊ ሆነ፡፡ በዚሁ መሥሪያ ቤት ለዘጠኝ ዓመት ያህል ሠርቷል፡፡ በኋላም ከ1983 የመንግሥት ለውጥ በኋላ ከዚሁ መሥሪያ ቤት ተሰናበት፡፡ ከስንብቱ በኋላ መጀመሪያ ናይስ ኢንሹራንስ ኩባንያ የሕዝብ ግንኙነት መኮንን በመሆን ለአንድ ዓመት ሠራ፤ በመቀጠልም በግሉ መንቀሳቀስ ጀምሮ “ሳን” የሚባል የማስታወቂያ ድርጅት በማቋቋም ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከዚያ ደግሞ እንቁጣጣሽ፣ ልደትና ፋሲካ የሚሉ የማስታወቂያ ጋዜጦች ማዘጋጀት ጀምሮ ነበር፡፡ ከድርጅቶች ማስታወቂያውን በመጠየቅ በአንድ ጎን ንባቡን በአንድ ጎን ደግሞ ማስታወቂያውን በማውጣት ሰፊ ተነባቢነት የነበረውን ጋዜጣ ነበር፡፡

ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ በኮንትራንት እየሠራ በዚሁ ሬዲዮ ጣቢያ ተወዳጅ የሆነውን የራዲዮ መጽሔት ፕሮግራም በማዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡ ንጉሤ አክሊሉ ከጋዜጠኝነት ሕይወቱ በተጨማሪ ዜማዎችን በመድረስ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሀገርን የሚመለከቱ፣ የሕዝቡን ባሕልና ጀግንነት፣ ታሪኳን የተመለከቱ ወደ 20 የሚደርሱ ዜማዎችን አዘጋጅቷል፡፡

 በእነዚህና በሌሎች ለሀገራቸው በሠሯቸው ሥራዎች ምክንያት በዳኞች ውሳኔ በ2009 ዓም በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ ዘርፍ የዓመቱ በጎ ሰው ተሸላሚ ሆነዋል፡፡