ተስፋዬ ገሠሠ

በኪነ ጥበብ(ቴአትር) ዘርፍ 2009 የበጎ ሰው ተሸላሚ

 

ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ተርጓሚ፣ መምህር፣ ፀሐፌ- ተውኔት . . .

በኢትዮጵያ የዘመናዊ ቴአትር ታሪክ ከሚጠቀሱ የዕድገቱ መነሻዎች አንዱ፡፡

1931 ሐረር ጉሮ ጉቱ ተወለደ፡፡ ቴአትርን የጀመረው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ ነው፡፡ በዚያ ያሳየው እንቅስቃሴ ለስከኮላርሺፕ አብቅቶት አሜሪካን ሀገር ኖርዝ ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ በ1950ዎቹ መጨረሻ ለትምህርት ሄደ፡፡ ከአሜሪካን ሀገር ሲመለስ ቴአትር የባላባቶቹ መጨዋቻ ከመሆን ወጥቶ ቅርጽና መልክ ያለው የኪነ ጥበብ ዘርፍ እንዲሆን ከሚጥሩት አዳሾች ጋር ተቀላቀለ፡፡ እኤአ በ1960 የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትርን ተቀላቀለ፡፡ በዚያም በከተማ ሕይወት ላይ ያተኮረውን የሺየተባለውን ቴአትር አቀረበ፡፡

በ1966 የሀገር ፍቅር ቴአትር ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ተሾመ፡፡ በ1967 ዓ.ም. ደርግ ከሥልጣኑ አውርዶ ወደ ወኅኒ አገባው፡፡ የዚህ መነሻው ዕቃውበተሰኘው ቴአትሩ መንግሥታዊ ሽብርን በመተቸቱ ምክንያት ነበር፡፡ በ1968 ዓ.ም. የብሔራዊ ቴአትር ሠራተኞች ባደረጉት ሰልፍ ጸጋዬ ገብረ መድኅን ከብሔራዊ ቴአትር ሥራ አስኪያጅነቱ ሲሰናበት ተስፋየ ገሠሠ በቦታው ተተካ፡፡

ፀረ ኮሎኒያሊስትየሚለውን በማዘጋጀቱና የራሱን ቴአትር ተሐድሶየተሰኘውን በማቅረቡ የተስፋዬ ገሠሠ አከራካሪነት ቀጠለ፡፡ ይህ አከራካሪነቱ እየባሰ ሄዶ እኤአ በ1979 ዓም ተባረረ፡፡ ከተባረረም በኋላ በ1980ዎቹ ፖለቲካ ቀመስ ቴአትሮቹን ጽፏል፡፡ Cherchez Les Femmes', ፍርዱን ለናንተ፣ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ሀገር ፍቅርን ባስተዳደረበት ጊዜ፤ ግቢውን አስፓልት አስነጥፏል፣ ኢንሹራንስ እንዲገባ አድርጓል፣ ቴአትር ቤቱን አሳድሷል፡፡

ተስፈዬ ገሠሠ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለብዙ ዓመታት አስተምሯል፡ ቤተ ኪነ ጥበብ ወቴአትርን ካቋቋሙት አንዱ ነው፡፡ ከኦኬስትራ ኢትዮጵያ መሥራቾችም አንዱ ነበር፡፡ በቴአትር ሞያው ብቃት ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የእጅ ሰዓት ተሸልሟል፡፡

ተሐድሶ፣ ዕቃው፣ ዱላው፣ እና በርካታ ቴአትሮችን ጽፏል፡፡በ ሐምሌት እና ከ20 በላይ ተውኔቶች ላይ ተጫውቷል፡፡

የተለያዩ መጻሕፍቶችን ጽፏል፣ ተርጉሟል፡፡ ከእነዚህ መካከል መተከዣየተሰኘው ታዋቂ ነው፡፡

በቴአትር ዓለም ወጣቶች መንገዱን እንዲከተሉ በማበረታታት፣ በማስተማር፣ በተጠራበት ቦታ ተገኝቶ ሐሳብ በመስጠትና ሞያው እንዲታወቅና እንዲከበር በማድረግ የበኩሉን ግዴታ ተወጥቷል፡፡

በእነዚህና በሌሎች ለሀገራቸው በሠሯቸው ሥራዎች ምክንያት በዳኞች ውሳኔ በ2009 ዓም በኪነጥበብ (ቴአትር) ዘርፍ የዓመቱ በጎ ሰው ተሸላሚ ሆነዋል፡፡