ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ንጉሤ ተበጀ

በሳይንስ ዘርፍ የ2009 የበጎ ሰው ተሸላሚ

እኤአ ኦክቶበር 16 ቀን 1944 ተወለዱ፡፡ በ1965 በ.ኤስ ሲ. ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፤ በ1969 ኤም. ኤስ. ሲ ከሌይግ ዩኒቨርሲቲ(አሜሪካ)፣ በ1972 ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ ፒ.ኤች.ዲ አግኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል መሐንዲሶች ማኅበር፣ የአሜሪካ ሲቪል መሐንዲሶች ማኅበር፣ የረዣዥም ሕንጻዎች ካውንስል የቴክኒክ ኮሚቴ አባል (አሜሪካ)፣ ዓለም ዐቀፍ የድልድዮችና የስትራክቸራል መሐንዲሶች ማኅበር አባል ናቸው፡፡

በዚህ ሞያቸው በኢትዮጵያ፣ በአሜሪካ፣ በፈረንሳይ፣ በኡጋንዳ፣ በታንዛንያና ደቡብ ሱዳን ሠርተዋል፡፡ ከ1989 እስከ 2017 ድረስ ከአምስት እስከ 33 ፎቆችን የያዙ 39 ሕንጻዎችን ስትራክቸራል ዲዛይን፣ ከ300 ሜትር ኪዩብ 500 ኪዩቢክ በሚደርሱ አራት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ስትራክቸራል ዲዛይን ሠርተዋል፡፡ ከ1984 ዓም ጀምሮ ከ34 በላይ በሚሆኑ የሀገራችን ታላላቅ ግንባታዎች የስትራክቸራል ዲዛይኖች ላይ በልዩ ልዩ መልኩ ተሳትፈዋል፡፡ በተለይም ድልድዮች፣ ግድቦችና የመተላለፊያ ዋሻዎችን ዲዛይን በመሥራት፣ በማማከር፣ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች የመፍትሔ ሐሳብ በማመንጨት ላለፉት 35 ዓመታት ሀገራቸው አገልግለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በዚሁ የተካበተ ዕውቀታቸውና ልምዳቸው አያሌ ምሁራንን አፍርተዋል፡፡

ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ንጉሤ ተበጀ በሀገራችን የግንባታ ታሪክ ውስጥ በሦስት ነገሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ታላላቅ የድልድይና የግንባታ ሥራዎችን በማቀድ፣ በማማከርና ችግር በመፍታት፣ የታላላቅ የግንባታ ማሽኖችን ችግሮች በመፍታትና በዘርፉ ጥናትና ምርምር በማድረግ፡፡ ለምሳሌ እኤአ በ2006 የዓባይ ግድብን ለመገንባት የሚያገለግል ከባድ ማሽን ሲያጓጉዙ የነበሩ ሁለት ተሸከርካሪዎች የዓባይ ድልድይን ለማቋረጥ ለሦስት ሳምንታት ያህል ተቸግረው ነበር፡፡ የድልድዩ የመሸከም ዐቅም ይችላል ወይስ አይችልም የሚለውን መወሰን ባለመቻሉ፡፡ በመጨረሻ የፕሮፌሰር ንጉሤ ዕውቀት ነው ችግሩን ሊፈታው የቻለው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ምሕንድስናን በተመለከተ ሊጠቀሱ ከሚችሉ ችግር ፈቺ የሞያው ባለቤቶች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ንጉሤ ከ22 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን፣ ከ8 በላይ መጻሕፍትንና  ከ5 በላይ የሥራ ሕግጋትን (Code of Practice) ያቀረቡ ምሁር ናቸው፡፡ በልዩ ልዩ የዲዛይን ዳኝነቶች (Jury) ላይ ከመሳተፋቸውም በላይ ምሕንድስናን በተመለከተ አያሌ የግልግል ዳኝነቶችን ሰጥተዋል፡፡

በእነዚህና በሌሎች ለሀገራቸው በሠሯቸው ሥራዎች ምክንያት በዳኞች ውሳኔ በ2009 ዓም በሳይንስ  ዘርፍ የዓመቱ በጎ ሰው ተሸላሚ ሆነዋል፡፡