ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ

በማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ 2009 የበጎ ሰው ተሸላሚ

ባሕሩ ዘውዴ ታዋቂ የዘመናዊት ኢትዮጵያ የታሪክ ሊቅ ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ እኤአ በ1970 ዓም በከፍተኛ ማዕረግ ተቀበሉ፡፡ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት ከእንግሊዝ የሎንዶን ዩኒቨርሲቲ በ1976 ዓ.ም. ነው፡፡ ከ1970 – 1972 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ረዳት መምህር፣ ከ1981-1986 ረዳት ፕሮፌሰር፣ ከ1986-1994 ተባባሪ ፕሮፌሰር፣ በ1992 በአሜሪካ ኤሊኖይስ ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ ተባባሪ ፕሮፌሰር፣ ሆነው ካገለገሉ በኋላ በ1992 ሙሉ ፕሮፌሰርነትን ተቀዳጅተዋል፡፡ በ2002 ዓ.ም. ደግሞ የጀርመን ሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ ፕሮፌሰር በመሆንም አገልግለዋል፡፡ ከ2004 ጀምሮ ደግሞ ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ሆነው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር (1993-1996)፣ የታሪክ ክፍል ሊቀ መንበር (1982-86)፣ የማኅበራዊ ጥናት መድረክ አንዱ መሥራችና የአማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ (1998-2004)፣ የዚሁ የማኅበራዊ ጥናት መድረክ ዋና ዳይሬክተር (2005-2010)፣ የትረስት አፍሪካ የቦርድ አባል (2005-2014)፣ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የታሪክ ባለሞያዎች ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ አባል (1989-1993)፣ የአፍሪካ የታሪክ ባለሞያዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት (2001- አሁን)፣ የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሞያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት (1994-1997)፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት(2010-2016)፣ የምሥራቅ አፍሪካ የማኅበራዊ ጥናት ድርጅት (OSSREA) ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ማኅበር የቦርድ አባል (2010-2015) በመሆን አገልግለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት ዋና አዘጋጅ (1986-1996)፣ የምሥራቅ አፍሪካ የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት መጽሔት  አዘጋጅ (1999-2003)፣ የአፍሪካ መጻሕፍት ምልከታ መጽሔት ዋና አዘጋጅ (2004- እስካሁን)፣ ከማገልገላቸው በተጨማሪ የልዩ ልዩ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት አማካሪ ቦርድ በመሆን ሠርተዋል፡፡ ልዩ ልዩ ዓለም ዐቀፍ ኮንፈረንሶችን በዋናና ተባባሪ አዘጋጅነት አዘጋጅተዋል፤ ከሰባት በሚበልጡ አህጉራዊና ክፍለ አህጉራዊ የጥናት መስኮችም ተሳትፈዋል፡፡

ለዚህ ሰፊና ጥልቅ አገልግሎታቸውም የብሪቲሽ ቆንስላ ስኮላርሺፕን (1972-1976)፣ የብሪቲሽ አካዳሚ ፌሎውሽፕን (1983)፣ የፈረንሳይ መንግሥት የጥናት አምኃ (1986)፣ የጃፓን ፋውንዴሽን ፌሎውን (1991) የUSIA ተጋባዥ ባለሞያ በቦስተን ዩኒቨርሲቲ (1991)፣ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የመስቀሉ ኮሌጅና የቅዱስ እንጦንስ ኮሌጅ ተጋባዥ ባለሞያ (1992)፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የወርቅ ኢዮቤልዩ ሽልማት (2000)፣ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ መሥራች ፌሎው (2010- እስካሁን)፣ የበርሊን የዊሰንስካፍስ ኮሌጅ ፌሎው(2010-2011)፣ የአፍሪካ ሳይንስ አካዳሚ ፌሎው (ከ2015 ጀምሮ) ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የዘመናዊቷን ኢትዮጵያ ታሪክ በተመለከተ አያሌ ጥናታዊ ጽሑፎችን ከማቅረብ በተጨማሪ ተጠቃሽ የሆኑ መጻሕፍትንም አዘጋጅተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ 1848-1966፣ ሀብቴ አባ መላ ከጦር መኮነንነት እስከ ሀገር መሪነት፣ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ በ1903፣ የተሰኙ መጻሕፍትንም አዘጋጅተው ለአንባቢያን አቅርበዋል፡፡

ከእነዚህም በተጨማሪ ከ42 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን በልዩ ልዩ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ በዲክሽነሪ ኦፍ አፍሪካን ባዮግራፊ፣ በኢንሳይክሎፔድያ ኦፍ አኢቶፒካ ላይ ሰፊ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ አያሌ መጻሕፍትን ገምግመዋል፣ በብዙ ሕዝባዊ መድረኮችም እውቀታቸውን አካፍለዋል፡፡ በአጠቃላይ ፕሮፌሰር ባሕሩ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያጠኑ፣ የጻፉ፣ ያስተማሩና በልዩ ልዩ ብሔራዊና ዓለም ዐቀፋዊ ተቋማትም በመሪነትና በተሳታፊነት ያገለገሉ ታላቅ የታሪክ ባለሞያ ናቸው፡፡

 

በእነዚህና በሌሎች ለሀገራቸው በሠሯቸው ሥራዎች ምክንያት በዳኞች ውሳኔ በ2009 ዓም በማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ የዓመቱ በጎ ሰው ተሸላሚ ሆነዋል፡፡