ሸዋ ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ

በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ የ2009 የበጎ ሰው ተሸላሚ

አቶ ዘሙይ ተክሉ ቅስሙ ከዛሬ ሰባ ዓመታት በፊት ከአንድ ኢጣሊያዊ ዳቦ ቤት በመጀመሪያ ተቀጥረው ይሠሩ ነበር፡፡ በታታሪ ሠራተኝነታቸው የተነሣ ጣሊያናዊው ሥራውን መተው ሲፈልግ ለእሳቸው ሸጠላቸው፡፡ እሳቸውም ይህንን ዳቦ ቤት በመግዛት መርካቶ ጎጃም በረንዳ አካባቢ ልዩ ስሙ አባኮራን ሠፈር በሚባል ቦታ የዛሬ ስድሳ ዓመት በአነስተኛ የዳቦ ምርት ሥራ ጀምረው ለአገራችን ሕዝብ ዳቦ በሽያጭ ማቅረባቸው በኅብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት አስገኘላቸው፡፡ ሥራቸውንም አስፋፍተው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ፒያሳ፣ ደብረ ዘይት መንገድ፣ በላይ ዘለቀ መንገድ፣ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት የዳቦ መጋገሪያና መሸጫ ቤቶችን በመከፈት ማስፋፋት ቀጠሉ፡፡

ለዳቦ ምርት ግብአት የሚውል ዱቄት ከተለያዩ ዱቄት ፋብሪካዎች ከመግዛት ይልቅ እድገትን ስለተመኙ የራሳቸው ዱቄት ፋብሪካ እንዲኖራቸው ዓላማቸው ስለነበራቸው አዳማ(ናዝሬት) ከተማ አንድ ዱቄት ፋብሪካ ከግሪኮች በመግዛት ሥራቸውን አስፋፉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፖፖላሬ፣ ቦሌ ኦሎምፒያ አካባቢ፣ መሿለኪያ፣ ጎፋና በተለያዩ ቁልፍ ቦታዎች በመምረጥ ዳቦ ቤቶችን በማቋቋም ወጥና ጥራቱን የጠበቀ የተለያየ ዳቦ በመጋገር እጅግ በጣም በተመጣጣኝና ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በተመጣጣኝ በዋጋ በማቅረብ ላይ ያለ አንጋፋውን ሸዋ ዳቦና ዱቄት ፋብሪካን አሁን ያለበት ደረጃ አድርሰዋል፡፡

ሸዋ ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ 1200 (ከአንድ ሺሕ ሁለት መቶ) በላይ የሚሆኑ ሠራተኞች በመቅጠር የሥራ ዕድል የፈጠረ ድርጅት ሲሆን፤ ይህንን ዓላማውን አንግቦ የሙያ ሥርዐቱን በማጎልበት ለቀጣዩ ትውልድ አርአያ ለመሆን የሚጥር ድርጅት ነው፡፡

አቶ ዘሙይ ተክሉ ዕድሜያቸው ሲገፋ ለሚቀጥለው ትውልድ ልጆቻቸው ሰጥተው(በማስተላለፍ) በአሁኑ ወቅት ልጆቻቸው ይህንን ሥራ በአጥጋቢ ሁኔታ እየመሩና ቀድሞ ከነበረበት ደረጃ እጅግ በጣም በማሳደግ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዘመናዊና በሀገሪቱ ብቸኛ የሆነ የዳቦ መጋገሪያ ኢንዱስትሪ እንዲሁም ከዚህ ጋር የተያያዘ ለዳቦ መያዣ የሚሆን የፕላስቲክ ውጤት ፌስታል እያመረቱ ይገኛሉ፡፡

በዳቦ ምርት ዘርፍ ለትላልቅ የመንግሥት ተቋማት ሆቴሎችና ሌሎች የሸዋ ዳቦን የምርት ውጤቶች ለሚሹ ሁሉ ከማንም በላይ አቅርቦቱን እያስፋፋ የሚገኝ ድርጅትን በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡

በጎ አድራጎትና ልዩ ልዩ ተሳትፎዎችን በተመለከተ ከክፍለ ከተማዎች ከወረዳዎች ከልዩ ልዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች ሰፊ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ እንደ መቄዶንያ ላሉ የበጎ አድራጎት ተቋማትም ቋሚ ደጋፊ ነው፡፡

በእነዚህና በሌሎች ለሀገራቸው በሠሯቸው ሥራዎች ምክንያት በዳኞች ውሳኔ በ2009 ዓም በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ የዓመቱ በጎ ሰው ተሸላሚ ሆነዋል፡፡