አቶ ማሞ ከበደ ሸንቁጥ

በመምህርነት ዘርፍ የ2009 ዓም የበጎ ሰው ተሸላሚ

አቶ ማሞ ከበደ ሸንቁጥ በ 1930 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በአዲስ አበባ በወንድ ይራድ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ደግሞ በካቴድራል ትምህርት ቤት በማታው የትምህርት ክፍል ተከታትለዋል፡፡ በ 1953 ዓ.ም. ከደብረ ብርሃን መምህራን ማሠልጠኛ ተቋም በመምርነት ሞያ ተመርቀዋል፡፡ ከዚያም በ1963 ዓ.ም. ከቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ እ.አ.አ. በ 1981 በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ኒው ዮርክ ከሚገኘው ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ በኮሚዩኒኬሽን ዕቅድ እና ስልት በሰርቲፊኬት ተመርቀዋል፡፡

አቶ ማሞ ለስምንት ዓመታት ያህል በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመምህርነት እንዲሁም በርእሰ መምህርነት፤ ለሁለት ዓመታት ያህል ደግሞ በመምህራን ማሠልጠኛ ተቋም መምራንን በማሠልጠን፤ የዕጩ መምህራንን የተግባር ሥልጠና በማስተባበር እና የትምህርት አስተዳደር ዲን ሆነው በአዲስ አበባ የኮተቤ መምህራን ማሠልጠኛ ተቋምን በመምራት ጭምር አገልግለዋል፡፡

በተጨማሪም ለ 13 ዓመታት ያህል በሬዲዮና በቴሌቪዥን የተለያዩ የትምህርት መርሐ ግብሮችን እና የጎልማሶች እና ተከታታይ ትምህርትን ለማስማር የሚያገለግሉ መጻሕፍትን አዘጋጅተዋል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜም በትምህርት ሚኒስቴር የተለያዩ ክፍሎችን፤ የጎልማሶችና ተከታታይ ትምህርት ክፍልን ጨምሮ በበላይነት መርተዋል፡፡

አቶ ማሞ ከበደ 43 የሚሆኑ የምርምር ሪፖርቶችን እና አጫጭር ጽሑፎችን አዘጋጅተዋል፡፡ ሰባት የሚሆኑ ሃገር በቀል እና ዓለም አቀፍ ማኅበራት አባል ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ የግል፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን፤ ከኢትዮጵያ ውጭ ኡጋንዳን ጨምሮ ከመንግሥት ሥራቸው በተጓዳኝ በትምህርት ሥራ የማማከር እና አመራር አገልግሎት በመስጠት ከ 33 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡

አቶ ማሞ ለሃገራቸው ካበረከቷቸው የላቁ አስተዋጽዖዎች መካከል የብሔራዊ የመሠረተ ትምህርት ዘመቻን ማሳካታቸው በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ አቶ ማሞ የብሔራዊ መሠረተ ትምህርት ዘመቻን በ15 ቋንቋዎች፣ ከሃያ አምሥቱ ዙሮች  አሥራ ሰባቱን ስልሣ ስምንት በመቶ ( 68%)  የሚሆነውን ብሔራዊ ዘመቻ መርተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በወቅቱ ከነበሯቸው የሥራ ሐላፊነቶች መካከል፤ ለሦስት ዓመታት በጎልማሶች ትምህርት እና በመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ጽ/ቤት የትምህርት መሣሪያዎች ዝግጅትና ሥርጭት ዋና ክፍል ሐላፊ፣ ለስምንት ዓመታት ደግሞ የጎልማሶች ትምህርት መምሪያና የብሔራዊ ትምህርት ዘመቻ አስፈጻሚ መኮንን ሆነው አገልግለዋል፡፡

አቶ ማሞ ለብሔራዊ የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ የሚውሉ የትምህርት መሣሪያዎች ዝግጅት፤ 23 ሚሊዮን የሚሆኑ መጻሕፍትን በ15 ቋንቋዎች በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ እንዲታተሙና እንዲሠራጩ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ እንዲሁም አጠቃላይ የትምህርት አሰጣጡን ሒደት በማስተባበር፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከመሃይምነት እንዲላቀቁ በማድረጉ ሒደት ከፍተኛውን አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡ በዚህ ብሔራዊ የትምህርት ዘመቻ የመረጃ ምንጮች እንደሚያመለክቱት 17 ሚሊዮን ተሳታፊዎች ከመሃይምነት ተላቀዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አርባ ሰባት በመቶ (47%) የሚሆኑት ሴቶች እንደነበሩም ተመልክቷል፡፡

ከሥልጠና በኋላ በየጊዜው በተደረገ የማንበብ እና የመጻፍ ምዘና ፈተና ከዘጠና በመቶ (90%) በላይ የሚሆኑት ተሳታፊዎች ፈተናውን በማለፋቸው የብሔራዊ መሠረተ ትምርት ዘመቻው ግቡን እንደመታ ተረጋግጧል፡፡ በወቅቱም በሃገሪቱ የነበረው የመሃይምነት መጠን፤ በ 1966 ዓ.ም.  ከነበረው ዘጠና ሦስት በመቶ (93%) በ1978 ዓ.ም. ወደ ሃምሣ በመቶ (50%) መውረዱን የመረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ፤ ከመንግሥት ሥራቸው በጡረታ ከተገለሉበት ከ1983 ዓ.ም.  ጀምሮ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ትምህርት እንዲያገኙ የሚያስችለውን ጥረት ቀጥለዋል፡፡ በ1984 ዓ.ም. የጎልማሶች መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ማኅበር በኢትዮጵያ  የተባለ አገር በቀል ድርጅት በማቋቋም ለአሥር ዓመታት መርተዋል፡፡ ይህ ድርጅት የትምህርት ዕድል ያላገኙ ጎልማሶች (ሴቶችን ጨምሮ) እና የትምህርት ተደራሽነት አነስተኛ በሆነባቸው የአርብቶ አደር ማኅበረሰቦች ለአኗኗር ዘይቤአቸው አመቺ የሆነ የትምህርት ዕድል ፈጥሮአል፡፡ ይህ እንዲሆን ካስቻሉት ሒደቶች መካከል፤ የመማር ማስተማር ቁሳቁስ ማደራጀት፣ የትምህርት መስጫ ማዕከሎችን ማቋቋም እና አጠቃላይ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓቱን መዘርጋት እና መምራትን ይጨምራል፡፡ ለእነዚህ ተግዳሮቶች ደግሞ የአቶ ማሞ አነሣሽነት እና አመራር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ ሌሎች መንግሥታዊ የሆኑ እና ያልሆኑ ተቋማትም ከዚህ አቀራረብ ጠቃሚ ትምህርት ወስደውና ልምድ ቀስመው፤ ተመሳሳይ መርሐ ግብሮችን አስፋፍተው እየተገበሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

አቶ ማሞ ከበደ ሸንቁጥ ላለፉት 35 ዓመታት ያህል በመላው ኢትዮጵያ ለታየው የትምህርት ተደራሽነት ስኬት እና በቦታ እርቀት እና በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ተገልለው ለነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የትምህርት ዕድል ማግኘት እጅግ ከፍ ያለ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ ከኢትዮጵያም ባሻገር በአፍሪካ ደረጃ ጠቃሚ የሆነ የመሠረተ ትምህርት እና የተከታታይ ትምህርት መማሪያ መጻሕፍትን በሦስት የውጪ ቋንቋዎች ሥልጠናና የዝግጅት ሥራውን በመምራትና በማስተባበር ጭምር በሐላፊነት አዘጋጅተዋል፡፡

በእነዚህና በሌሎች ለሀገራቸው በሠሯቸው ሥራዎች ምክንያት በዳኞች ውሳኔ በ2009 ዓም በመምህርነት ዘርፍ የዓመቱ በጎ ሰው ተሸላሚ ሆነዋል፡፡