የ2008 ተሸላሚዎች ዝርዝር

በመምህርነት ዘርፍ

መምህር አውራሪስ ተገኝ

መምህር አውራሪስ ተገኘ የካቲት 27 ቀን 1959 ዓ.ም በጎጃም ክፍለ ሀገር ተወለዱ፡፡ ከጎንደር መምህራን ኮሌጅ በሂሳብትምህርት ዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ ከደብረ ብርሃን መምህራንኮሌጅ የርዕሰ መምህርነት ስልጠና ወስደዋል፡፡ ከአዲስ አበባዩኒቨርስቲ ንግድ ሥራ ኮሌጅ በቢዝነስ አስተዳደርና ቴክኖሎጂበባችለር ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ ከ1979 ዓ/ም ጀምሮ ለ18 ዓመታት በመምህርነት ሙያ

ያገለገሉት አቶ አውራሪስ ባስተማሩባቸው አካባቢዎች ለትውልዱ የዕውቀትን ወጋገን አብርተዋል፡፡ መንግሥት “የመጀመሪያ ደረጃትምህርትን ለሁሉም ማዳረስ” የሚል የሚሊኒየም የልማት ግብከማስቀመጡ አስቀድመው ባስተማሩባቸው ቃንጣ ባብጫየመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት፣ ከበሴ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት፣ዓለማየሁ በዛብህ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ባሉባቸው አካባቢዎች ‹ትምህርት ለሁሉም ሕፃናት› የሚል እቅድ በመቅረፅበ1980ቹ መጨረሻ ሁሉም ሕፃናት እንዲማሩ አድርገዋል፡፡

ለሰዎች በጎ በማድረግ የሚደሰቱት አቶ አውራሪስ የአርሶአደር ልጆችን በየገጠሩ በመዞር፤ እስከ ሁለት ቀን የእግር ጉዞበመጓዝ እና በአርሶ አደሮች ቤት በማደር፤ ከአርሶ አደሮች ጋርየጠበቀ ጓደኝነትና ማኅበራዊ ትስስር በመፍጠር፣ አርሶ አደሮችልጆቻቸውን ወደ ትምህርት እንዲልኩ የማሳመን ስራዎችንበመስራት በቆዩባቸው የአንደኛ ደረጃ ርዕሰ መምህርነት ሙያበእርሳቸው በጎ ተፅዕኖ ከ15 ሺህ ህፃናት በላይ ከመሃይምነት ነፃአውጥተዋል፡፡ ከህፃናት በተጨማሪ በቢቡኝ ወረዳ በግብርና ሙያየተሰማሩ አርሶ አደሮች እና በጥንታዊ የአብነት ት/ቤት የሚማሩተማሪዎች ጎን ለጎን ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ አድርገዋል፡፡በወረዳው የማኅበረሰብን እሴት በመጠበቅ ማኅበረሰቡ ለዘመናዊትምህርት የነበረውን አሉታዊ ግንዛቤ ሙሉ በሙሉ ቀይረዋል፡፡

ለማስተማር አቅም የሌላቸውን አርሶ አደሮች ልጆቻቸውንቤታቸው ይዘው በማሳደግ አስተምረዋል፡፡ ለአካል ጉዳተኛህፃናትም ለመንቀሳቀሻ አጋዥ መሳሪያ በመግዛት በርቀትምክንያት ከትምህርት እንዳይቀሩ አድርገዋል፡፡ ከዚህየሚተርፋቸውን የወር ደመወዝ ለተማሪዎቻቸው የኩራዝመብራት የሚሆን ናፍጣ ገዝተው በመስጠት ጠንክረውእንዲያጠኑ በፅናት ይመክሩ ነበር፡፡ ሌሊት በቢቡኝ ወረዳ ባሉአርሶ አደር መንደሮች በመዞር ተማሪዎቻቸው እየጠኑመሆናቸውን ይቆጣጠሩ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኛውየቀለም ልጆቻቸው በአገር ውስጥና በውጭ ዩኒቨርስቲዎችበከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡

በቡቡኝ ወረዳ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ባለመኖሩ ተማሪዎችአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸው ከጨረሱ በኋላ ብዙ ርቀት ተጉዘውበብዙ ችግር ይማራሉ፡፡ አልያም ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ፡፡ይህን ችግር ለመፍታት አቶ አውራሪስ ተገኝ በጎ አድራጊለማፈላለግ በእግራቸው ተጉዘዋል፣ ቤታቸውን ሸጠዋል፡፡በመጨረሻም አቶ ዘውዴ ከተባሉ ግለሰብ ብር 3.5 ሚሊዮን ብርድጋፍ ተደርጎላቸው ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቱ እንዲሰራ አድርገዋል፡፡አቶ አውራሪስ የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር ሁለት ቤተመጻሕፍት አሰርተዋል፡፡ ከ30 በላይ የሚሆኑ ወላጆቻቸውን ያጡህፃናትን አሳድገዋል፡፡

መምህር አውራሪስ ተገኝ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለሕዝብ በሚጠቅሙ የላቀ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሠረት በመምህርነት ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡ 

 

በንግድና ስራ ፈጠራ ዘርፍ

አቶ ሳሙኤል ታፈሰ

አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ቂርቆስ አካባቢ ከችግረኛ ቤተሰብየተወለዱ ኢትዮጵያዊ የቢዝነስ ሰው ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በፈለገ ዮርዳኖስ ት/ቤት እየተማሩ ሳለበልጅነታቸው ጥቃቅን የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ቤተሰቦቻቸውንና ራሳቸውን ከመደገፍ ጀምረው አሁን ላሉበትትልቅ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ አቶ ሳሙኤል የዛሬ በ1977 ዓ.ምከሰዎች 10,000 ብር ተበድረው ደረጃ 9 ንግድ ፈቃድአውጥተው ሥራቸውን በሕንፃዎች ቀለም እና በጣራ እድሳትጀምረው ንግዳቸውን አስፋፍተዋል፡፡

አቶ ሳሙኤል በአሁኑ ሰዓት ከ6,200 በላይ ሠራተኞችንየሚያስተዳድረው የሰንሻይን ኮንስትራክሽን የግል ማኅበርባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ ድርጅቱ በዋናነት በኮንስትራክሽንኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርቷል፡፡ ድርጅቱ በቡታጅራ ቡሬያቤሎ እና የቤንሻንጉል ጉምዝ አካባቢዎች አጅግ አስቸጋሪየሆኑና ተራራማ መንገዶችን በመስራት ከ15 በላይ የሚሆኑየመንገድ ፕሮጀክቶችን አሳክተዋል፡፡ ድርጅቱ አሁንም በግዙፍየመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ላይ ነው፡፡

አቶ ሳሙኤል በሪል እስቴት ዘርፍ በመሰማራትም በገርጂ፣መሪ፣ እና CMC (ሲኤምሲ) አካባቢ የጋራ አፓርትመንቶችንናቪላ ቤቶችን እየሰሩ ለህብረተሰቡ አቅርበዋል፡፡ ሰንሻይን ግሩፕወደ ሆቴል ኢንቨስትመንት በመግባትም ማሪዮት ኤክስኪዉቲቭአፓርትመንት ኢንተርናሽናል ሆቴልን በአዲስ አበባ እዉን ያደረገሲሆን ማሪዮት ሆቴልን በአዲስ አበባ፤ ሒልተን ሆቴልን ደግሞበአዋሳ ለመገንባት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

አቶ ሳሙኤል የዜግነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በበጎአድራጎት ሥራ በመሰማራት ሰንሻይን ፋውንዴሽንን በማቋቋምመማር ለማይችሉ ወገኖች (ህፃናት) ት/ቤት ከፍተዉ በማስተማርላይ ናቸው፡፡

  • በነቀምት የዛሬ 8 ዓመት በ8,ሚሊዮን ብር ከ1-10ኛ ክፍልየሚስተምር ት/ቤት በመገንባት 400 ተማሪዎች በመቀበልለህፃናቱ በየወሩ 200 ብር የኪስ ገንዘብ እየከፈሉ ያስተምራሉለህፃናቱም አስፈላጊውን ዩኒፎርምና የትምህርት መረጃያቀርባሉ፡፡
  • በአክሱም 400 ልጆች የሚማሩበት ት/ቤት በ11,ሚሊዮን ብርከፍተው በየወሩ 200 ብር የኪስ ገንዘብ እየሰጡ ያስተምራሉ፡፡
  • በጉራጌ ዞን በ18,ሚሊዮን ብር ት/ቤት አቋቁመው 350 ልጆችንበማስተማር ላይ ናቸው፡፡ በየወሩ 200 ብር የኪስ ገንዘብ እየሰጡያስተምራሉ፡፡
  • በደብረ ብርሃን አንኮበር አካባቢም 4ኛውን ት/ቤት ለመሥራትበዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

በተጨማሪም አዲስ አበባ ላይ 30,000 ካሬ ሜትር ወስደው በ35ሚሊዮን ብር የአረጋውያን መንደር በመሥራት ላይ ሲሆኑ 400አረጋውያንን ለመርዳት አቅደዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም የአረጋውያንመንደሩን ለመጨረስ ታቅዷል፡፡ እንዲሁም በግሼን ሌላኛውየአረጋውያን መንደር በመስራት 600 አረጋውያንን ለማቀፍእየተንቀሳቀሱ ነው፡፡

አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለሕዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሠረት በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡

በማህበራዊ ጥናት ዘርፍ

ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ

መኖሪያቸውን በአሜሪካ ያደረጉ ኢትዮጵያዊ የግዕዝ ጥናቶች ባለሞያ ናቸው፡፡ ዊኪፒዲያ ‹widely considered the foremost scholar of the Ge'ez language alive today.› ይላቸዋል፡፡ የተወለዱት ግንቦት 24 ቀን 1924 ዓም በሰሜን ሸዋ ሸንኮራ ሲሆን እኤአ ከ1945- 1951 ድረስ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተምረዋል፡፡ አኤአ በ1957 ከኮፕቲክ የነገረ መለኮት ኮሌጅ (ካይሮ፣ ግብጽ) በባችለር ኦፍ ዲቪኒቲ የተመረቁ ሲሆን በዚያው ዓመት በካይሮ ከሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ በቢ. ኤ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ እኤአ በ1962 ደግሞ ጀርመን ቱቢንገን ከሚገኘው ከኤበርሃርድ ካርልስ ዩኒቨርሲቲ (Eberhard Karls University, Tübingen) በሴማውያን ቋንቋዎች ፊሎሎጂ የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያን ጥንታዊ የብራና ጽሑፎች በማጥናት፣ የካታሎግ ሥራ በመሥራትና በጉዳዩ የሚያጠኑትን በማማከር ይታወቃሉ፡፡ በሚኒሶታ የቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ ሪጀንተስ ኤሚሪተስ ፕሮፌሰር ሲሆኑ በሂል ሙዝየምና የብራና መጻሕፍት ቤተ መጻሕፍት ደግሞ ኪዩሬተር ኤሚሪተስ ናቸው፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (አዲስ አበባ) ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል በተባባሪ ፕሮፌሰርነት እኤአ ከ1962-1969፣ እንዲሁም ከ1971-1974 ዓም የአማርኛ ሰዋሰው፣ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ፣ የግዕዝ ሰዋሰው፣ የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ፣ የዐረብኛ ሰዋሰው እና የሴም ቋንቋዎችን ሰዋሰው አስተምረዋል፡፡

እኤአ በ1976 ዓም በሂል ሙዝየምና የብራና መጻሕፍት ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ሥራ ጀመሩ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከ5000 የሚበልጡ የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍትን በማጥናትና ካታሎግ በማድረግ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን የብራና መጻሕፍት ካታሎግ ለሚያዘጋጁ ባለሞያዎች፣ የፓልግራፊ (paleography) የተጻፉበትን ዘመን መወሰን (dating) እና ሌሎች ሥልጠናዎችን ሲሰጡ ኖረዋል፡፡ በእነዚህ ዘመናትም የተለያዩ የጥናት መጽሔቶች የቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የግዕዝ ሀብታችንን በተመለከተ በታወቁ ዐለም ዐቀፍ የጥናት መጽሔቶች ላይ ከ200 በላይ የጥናት ጽሑፎችን ያበረከቱ ሲሆን አያሌ መጻሕፍትንም በአማርኛና በእንግሊዝኛ አዘጋጅተዋል፡፡ አማርኛ መማሪያ ለጎልማሶች፣ አማርኛ መማሪያ ለጎልማሶችና ለመምህራን፣ አንዳፍታ ላውጋችሁ፣ ባሕረ ሐሳብ፣ ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ ሐተታ ዘርአ ያዕቆብ፣ ግዕዝ በአዲስ ዘዴ (ግዕዝ በቀላሉ)፣ የአባ ባሕርይ ድርሰቶች በአማርኛ ካዘጋጇቸው መካከል የሚተቀሱት ናቸው፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የጥናት ጽሑፎች አዘጋጅተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለሕዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሰረት በማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡

በሳይንስ ዘርፍ

ሎሬት ዶክተር መላኩ ወረደ

ሎሬት ዶክተር መላኩ ወረደ የተወለዱት አዲስ አበባ ነው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በእርሻ ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንና ዶክትሬታቸውን ደግሞ በ(Genetics and Plant Breeding) ከአሜሪካ አግኝተዋል፡፡ በአምቦ በሐሮማያ እና በጂማ የግብርና ኮሌጆች በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን ወንጂ ስኳር ፋብሪካ በተመራማሪነት ተቀጥረው በሚሠሩበት ወቅት ‹አረማሞ› በመባል ለሚታወቀውና ምርት ያስተጓጉል ለነበረ በሽታ መፍትሔ ያገኙ ሳይንቲስት ናቸው፡፡ በዶክትሬት ጥናታቸው በዓለም ላይ በሚገኙ አራት ሺሕ የስንዴ ዝርያዎች የፕሮቲን ይዘት ላይ ምርምር አድርገው አራቱን በጣም ምርታማ የሆኑትን ለይተዋል፡፡ ከአራቱ ሦስቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ፖርቱጋል ውስጥ የሚበቅለው አራተኛውም ከኢትዮጵያ የተወሰደ ነው በሚል ታሪክ ጠቅሰው ሞግተዋል፡፡ በዚህና በተለያዩ አጋጣሚዎች ከኢትዮጵያ የተዘረፉ ናቸው በሚሏቸው የብዝኃ ሕይወት ላይ በዓለም መድረኮች ሁሉ ሽንጣቸውን ገትረው በሚያደርጉት ሙግት ይታወቃሉ፡፡

ሎሬት ዶ/ር መላኩ ወረደ በወቅቱ የመጀመሪያውና ብቸኛው የነበረውን የዛሬውን የብዝኃ ሕይወት ኢንስቲቲዩትና የዚያኔውን የኢትዮጵያ ዕፅዋት ጀነቲክ ሀብት ኢትዮጵያን በጠቅላላ ዞረው ያላትን የብዝኃ ሕይወት በማሰባሰብ ተቋሙን መሠረት አስይዘው አቋቁመውታል፡፡ ዛሬ ተቋሙ ያሠራውን ሕንፃም በስማቸው ሰይሞታል፡፡ ሎሬት ዶ/ር መላኩ ወረደ በተጨማሪም የሐዋሳ ግብርና ኮሌጅ መሥርተው ለረዢም ዓመታትም በመምህርነትና በዲንነት አገልግለዋል፡፡

በአገራችን የሚገኘው ነባር የሰብል ዘር ከመጥፋቱ በፊት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የማንበር ዘዴና የምርምር ተግባራት በተጨማሪ በገበሬው ማሳ ላይ ማንበርና ምርታማነቱን ብሎም ተመራጭነቱን ተጓዳኝ የሚያደርግ A Dynamic Farmer Based Land Race Conservation and Utilization የተባለ አሠራር በዓለም ብቸኛው በመሆን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ ይህ ዘዴ ከአገራችን አልፎ በመልማት ላይ ባሉ በርካታ አገሮች በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡

ሎሬት ዶ/ር መላኩ ወረደ ከአብዛኛው ሳይንስቶች የሚለያቸውና ብዙ ጊዜም በአደባባይ ሲናገሩ የሚደመጡት ‹‹ለገበሬው ዕውቀት ቦታ መሰጠት አለበት፤ እነርሱን ማዳመጥ አለብን፤›› በሚለው አመለካከታቸው ነው፡፡ ‹‹ሳይንቲስቱ የራሱን ግኝት እነርሱ ላይ መጫን ሳይሆን የእነርሱን ባህላዊ አሠራር መሠረት አድርጎና አቀናብሮ መጓዝ ያስፈልጋል›› በሚለው አቋማቸውና ተግባራቸው ይታወቃሉ፡፡

ሎሬት ዶ/ር መላኩ በግብርናው መስክ ባደረጉት ምርምር (Alternate Nobel) ተብሎ የሚታወቀውን የ(Livelihood Award) ያገኙ ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት ናቸው፡፡ ሎሬት ዶ/ር መላኩ ከ20 የበለጡ ጥናቶች በአለማቀፍ ጆርናሎች በመጽጻሕፍት እና በልዩ ልዩ መልኩ አሳትመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሕመም ምክንያት ከቤት መንቀሳቀስ ባይችሉም ምክራቸውንና እርዳታቸውን የሚፈልጉ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ተቋማትን በምክራቸው እያገዙ ይገኛሉ፡፡

ሎሬት ዶ/ር መላኩ ወረደ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሰረት በሳይንስ ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡

በቅርስና ባህል ዘርፍ

ኢንጂኒየር ታደለ ብጡል ክብረት

ኢንጂኒየር ታደለ ብጡል የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ በ1919 ዓ.ም ነው፡፡ አራት ኪሎ በሚገኘው በዐለ ወልድ ቤተክርሰቲያን መንፈሳዊ ትምህርት እስከ ዳዊት ድረስ ተምረዋል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ የአስኳላ ትምህርታቸውን ቀድሞ ባላባትና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ይባሉ በነበሩ ትምህርት ቤቶች ተምረዋል፡፡ ወደ ሀገረ አሜሪካም አቅንተው በስትራክቸራል ዲዛይን በሲቪል መሐንዲስነት ሙያ ተመርቀዋል፡፡ በዚህ ሙያቸውም በአገር ውስጥና በውጭ አገራት በርካታ የግንባታ ሥራዎች ላይ ተካፋይ ሆነዋል፡፡ የምህንድስና ትምህርት ከመማራቸው አስቀድመው በባንክ ባለሙያነት ለስምንት ዓመታት አገልግለዋል፡፡

ኢንጂኒየር ታደለ ብጡል በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የማታ ትምህርትን ያስጀመሩ ናቸው፡፡ በታዋቂው አርበኛ የተሰየመውን ወንድይራድ ትምህርት ቤትን ከሌሎች ጋር በመሆን አቋቁመዋል፡፡ በድርሰቱም ዘርፍ በደራሲ ከበደ ሚካኤል፣ በዐፄ ቴዎድሮስ፣ በልዑል ዓለማየሁ፣ በሐኪም ወርቅነህ እሸቱ ላይ ከጻፏቸው መጻሕፍት በተጨማሪ የአማርኛ የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላትን በማዘጋጀት ይታወቃሉ፡፡ በአጠቃላይ ከአስራ አምስት በላይ መጻሕፍትን አዘጋጅተዋል፡፡

ኢንጂኒየር ታደለ ብጡል የተለያዩ ባሕላዊ እና ትውፊታዊ ቅርሶችን ከተለያዩ ክፍላተ ዓለማት በራሳቸው ወጪ በመግዛት በመሰብሰብ ይታወቃሉ፡፡ የሰበሰቧቸውን ቅርሶችንም በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ልዩ ልዩ ሙዚየሞች በመለገስ ታሪካዊ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ የአክሱም ሐውልት ብሔራዊ አስመላሽ ኮሚቴ አባል በመሆንም የተለያዩ ኃላፊነቶችን ወስደው ሰርተዋል፡፡ ሐውልቱን ለማስመለስ ከሌሎች ጋር በመሆን ከአስራ ሰባት ዓመታት በላይ ታግለዋል፡፡ ኢንጂኒየር ታደለ የአክሱም ሐውልትን ለማስመለስ እንደ አርበኛም ጣሊያኖችን በመከራከር፣ እንደ ባለ ሀብት በገንዘባቸው፣ እንደ ምንሕድስና ባለሙያነታቸው የሐውልቱን አመላለስ የምህድስና ጉዳዮች አጥንቶ እንዲተገበር በማድረግ በወርቅ ቀለም የደመቀ ታሪክ ለመጻፍ በቅተዋል፡፡ በተጨማሪም ከአክሱም ሐውልት መመለስ ጋር ተያይዞ “ኢትዮጵያዊ ፅናት” የተሰኘ ዶክመንተሪ ፊልም እና 640 ያህል ገፆች ያሉት መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡

ኢንጂኒየር ታደለ ብጡል ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው በዳኞች ውሳኔ መሰረት በቅርስና ባህል ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡  

መንግስታዊ ሃላፊነትን በብቃት በመወጣት ዘርፍ

ዶክተር ተወልደብርሃን ገብረ እግዚአብሔር

ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር የካቲት 11 ቀን 1936 ዓ.ም ትግራይ ተወልደው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት አካባቢ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ እንዲሁም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በባይሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልመው አጠናቀዋል፡፡ በመቀጠል ወደ እንግሊዝ ሄደው ከዌልስ ዩኒቨርሲቲ በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡

ከዚያም በ1961 ዓ.ም ወደ አገራቸው ተመልሰው በዩኒቨርሲቲ መምህርነትና በሳይንስ ፋኪልቲ ዲንነት፣ ሰርተዋል፡፡ ወደ አስመራ ዩኒቨርሲቲ ተልከው በፕሬዘዳንትነት ለስምንት ዓመታት በከፍተኛ ኃላፊነት መርተዋል፡፡ ከ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ በኋላም የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ስትራቴጂ ሴክሬታሪያት ዳይሬክተር ቀጥሎም የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡

ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር በሥነ ሕይወትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ከ30 በላይ ጥናቶችን በማሳተም፣ የአካባቢ ጥበቃ ስትራቴጂ በመቅረጽ፣ የሥነ ሕይወት ሀብታችንን የሚገልጹ መጽሐፎችን በማሳተምና በመሳሰሉት ለሀገርና ህዝብ የሚጠቅሙ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ከዚህ አልፈው በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ ማኅበረሰብ፣ ገበሬዎችና ከብት አርቢዎች የሥነ ሕይወት ሀብት ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ሕግ በተጨማሪም የአፍሪካን የባዮ ቴክኖሎጂ ሴፍቲ ሕግ በማርቀቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃም አገራችንንና አፍሪካን በመወከል በብዝኃ ሕይወትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ በተመረኮዙ የተለያዩ ድርጅቶች ላይ በግንባር ቀደምትነት ተሳትፈዋል፡፡ በተለይ ጂ 77 ተብለው ለሚታወቁ ሀገሮች ዋንኛ ተከራካሪ ሆነው በመሪነት በተጫወቱት ሚና በሥነ ሕይወት ደኅንነትና ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ እንዲከበር፣ ታዳጊ ሀገሮች አገር በቀልና የማህበረሰብ መብቶች እንዲከበሩ ሽንጣቸውን ገትረው ተከራክረዋል፡፡ በታሪክ የተመዘገቡ ውጤቶችንም አስመዝግበዋል፡፡

ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር በአገራችን የአካባቢ ሥነ ሕይወትና ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ጉዳይ ሲነሳ ከማንም በላይ በታላቅ ክብር ስማቸው የሚነሳ የተከበሩ ሳይንቲስት ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም በብዙ የምርምርና የትምህርት ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ታዋቂ ሰዎች ዘንድ የከበረ ስም አትርፈዋል፡፡ በተሰማሩበት መስክ የአገርንና የህዝብን ጥቅም በማስቀደም በተለይም የአርሶ አደሮችና የአርብቶ አደሮች ጥቅም እንዲጠበቅ በቁርጠኝነት ጠንክረው ሰርተዋል፡፡ በተዳቀሉ እህሎች በእርዳታ ሰበብ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡና ትውልድ እንዳይበላሽ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር ተከራክረዋል፡፡ በአጭር መግለጫ ተገልጾ በማያበቃው ሥራቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የክብር ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የአካባቢ ጥበቃ ሽልማት "የምድር ሻምፒዮን" ተብለው ተሸልመዋል፡፡

ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሰረት መንግሥታዊ ኃላፊነትን በመወጣት ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡

በስፖርት ዘርፍ

ዶክተር ይልማ በርታ

ከጉራጌ ዞን ምሁር የተገኙት የአትሌቲክስ አሠልጣኙ ዶ/ር ይልማ በርታ ገና የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደብረ ዘይት እየተከታተሉ ነበር ከስፖርት ጋር የተዋወቁት፡፡ የመረብ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ እና አትሌትክስን ቢያዘወትሩም በተለይ በሩጫው ዓለም በመካከለኛው ርቀት ሸዋን በመወከል ተወዳድረዋል፡፡

በጅማ መምህራን ማሠልጠኛ የመምህርነት ሥልጠና የወሰዱት ዶ/ር ይልማ ለሁለት ተከታታይ ክረምቶችም በደብረ ዘይት የሰውነት ማጎልመሻ ሥልጠና ወስደዋል፡፡ በደቦ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የቋንቋ አስተማሪ ተደርገው ቢመደቡም እርሳቸው ግን በትርፍ ሰዓታቸው ያሠለጥኑት የነበረውን ስፖርት የበለጠ ለማጠናከር ወደ ጅማ መምህራን ማሠልጠኛ ለተጨማሪ ሦስት ዓመት ከግማሽ ተመልሰው በመግባት የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት ተከታተሉ፡፡

በመስከረም 1974 ዶ/ር ይልማ በርታ በቺኮዝሎቫኪያ ቻርለስ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዕድል አገኙ፣ በቼክ ታዋቂው ዩኒቨርሲቲ የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርትን እየተከታተሉ ከ800 እስከ 1500 ሜትር ድረስ በመካከለኛ ርቀት ተወዳዳረው ጥሩ ውጤትን ለዩኒቨርሲቲው አስመዝግበዋል፡፡ የመጀመሪ ዲግሪያቸውን በአትሌቲክስ ያገኙት ዶ/ር ይልማ በርታ በዛው ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ለመሥራት ተቀባይነት አገኙ፡፡ የዶክትሬት ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በ1981 በስፖርት ኮሚሽን የመካከለኛ ርቀት አሠልጣኝ በመሆን ሥራ ጀመሩ፡፡ ወደ የመን በማቅናት የስፖርት አሠልጣኝ በመሆን የሠሩት ዶ/ር ይልማ በርታ ከየመን እንደ ተመለሱ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን የ5ሺህ እና 10 ሺህ አሠልጣኝ በመሆን በርካታ ጀግና አትሌቶችን አፍርተዋል፡፡

ዶ/ር ይልማ በርታ ለዓለማችን ካበረከቱዋቸው ታላላቅ አትሌቶች መካከል ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገ/ ሥላሴ ቀዳሚው ነው፡፡ የኢትዮዽያ አየር መንገድ ለዘረጋው የፓይለት ፕሮጀክት ከመለመሉዋቸው በርካታ አዳጊ አትሌቶች መካካል ኃይሌ ገብረ ሥላሴ አንዱ ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላም በኃይሌ ብቃት የተማረኩት ዶ/ር ይልማ ኃይሌን እና ሦስት ጓደኞቹን ለብሔራዊ ቡድን መረጡዋቸው፡፡ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በወቅቱ የ5 እና 10 ሺህ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ በነበሩት ዶ/ር ይልማ የሠለጠነው ኃይሌ በ1992 የደቡብ ኮሪያ የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5 እና 10 ሺህ አሸናፊ በመሆን ዓለምን በድል እንዲቀላቀል አደረጉት፡፡

በተለይ ከኃይሌ ጋር በርካታ ድሎችን ያጣጣሙት ዶ/ር ይልማ በሲዲኒ ኦሎምፒክ ከጉልበት ጉዳት ጋር እየታገለ ያሸነፈበትን ውድድር መቼም አይረሱትም፡፡ የብሔራዊ ቡድኑና የኃይሌ የማራቶን አሠልጣኝ በነበሩበት ወቅትም ኃይሌ በበርሊን ማራቶን የዓለም ሪከርድን እንዲሰብር አስችለውታል፡፡ የኢትዮዽን ቡድን በመምራትም በኦሎምፒክና በዓለም ሻምፒዮና በርካታ ወርቅ፣ ብርና የነሐስ ሜዳሊያዎችን በአሠልጠኝነት አግኝተዋል፡፡ በድል ያሸበረቀ ውጤታማ ታሪክ ያላቸው ዶ/ር ይልማ የተሰማቸውን በቀጥተኛ ተናጋሪነታቸውና ዕውቀታቸውን ለሌሎች በማጋራት ይታወቃሉ፡፡ በተለይ ከዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ ጋር ለረጅም ዓመት የሠሩት ዶ/ር ይልማ ‹በኮስትሬ ስኬት የተደበቁ ምርጥ አሰልጣኝ› ይሏቸዋል የስፖርቱ ተንታኞች፡፡ ከመካካለኛ ርቀት እስከ ማራቶን ብሎም በመሰናክል ሩጫ ውጤታማ መሆናቸውን በመጥቀስ ተገቢውን ክብር ያላገኙ ታላቅ ሰው ይሏቸዋል፡፡

ዶ/ር ይልማ በርታ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ የላቀ ተግባራቸው በዳኞች ውሳኔ መሰረት በስፖርት ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡  

 

በኪነ-ጥበብ /ድርሰት/ ዘርፍ

አቶ አውግቸው ተረፈ

አውግቸው ተረፈ የኅሩይ ሚናስ የብዕር ስም ነው፡፡ የተወለዱት በጎጃም ክፍለ ሀገር በቢቸና አውራጃ በ1942 ዓም ነው፡፡ ዋና ትምህርታቸው ነባሩ የቤተ ክህነት ትምህርት ነው፡፡ በስማቸው የተጻፉ ጥቂት መጻሕፍት ቢኖሩም በአንባብያን ዘንድ ጎልተው የወጡ ሥራዎቻቸው ግን በአውግቸው ተረፈ ስም የታተሙት ናቸው፡፡

አቶ አውግቸው መርካቶ አሮጌ መጻሕፍት መሸጥ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ አጫጭር ልብ ወለዶችን ኢ ልብ ወለድና የትርጉም ሥራዎችን፣ የሕጻናት ተረቶችንና መዝገበ ቃላት በማሰናዳት ከመታወቃቸውም በላይ ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እስከ ደርግ ዘመን መጨረሻዎቹ ዓመታት በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ በአርታኢነት አገልግለዋል፡፡

አቶ አውግቸው ተረፈ በትክክለኛ ስማቸውና በሌሎች የብዕር ስሞቻቸው ከሃያ በላይ መጻሕፍትን የደረሱና የተረጎሙ ሲሆን ለኅትመት ከበቁ ሥራዎቻቸው የሚከተሉት በአንባቢያን ዘንድ የታወቁ ናቸው፡፡ ከፈጠራ ሥራዎቻቸው መካከል ‹ወይ አዲስ አበባ› ‹ዕብዱ› እና ‹የፕሮፌሰሩ ልጆች›፣ ከትርጉም ሥራዎቻቸው መካከል የባልዛክ ‹ምስኪኗ ከበርቴ› የኦ.ሄንሪና የሌሎች ደራስያን ስብስብ የሆነውን ‹ያንገት ጌጡ›፣ የዳንኤላ ስቲል ‹ጽኑ ፍቅር› እና ‹ምስጢራዊቷ ሴት›፤ የሃሮልድ ሮቢንስ ‹ጩቤው› ሲገኙበት፣ ከኢ ልብወለድ ሥራዎቻቸው መካከልም በባቢሌ ቶላ የተጻፈው ‹የትውልድ ዕልቂት› ይገኝበታል፡፡

የአቶ አውግቸው መጻሕፍት ቀለል ባለ አቀራረብ ማኅበራዊ ሂስ የሚሰጡ የንባብን ፍላጎት የሚያነሳሱና በውጪው ዓለም ከፍተኛ ተነባቢነት ያገኙ እንዲሁም ዘመን አይሽሬ ከተሰኙ ደራስያን ተመርጠው የተተረጎሙ ናቸው፡፡

አቶ አውግቸው ተረፈ በአንድ ወቅት የደረሰባቸውን የእዕምሮ ሕመም መነሻ በማድረግ የጻፉት ‹ዕብዱ› የተሰኘው መጽሐፍ በአእምሮ ሕክምና ሰጪዎች ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱና ለተሻለ ጥናት ግፊት በማሳደሩ፤ የአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አውግቸው ይታከሙበት የነበረውን ሕንጻ በስማቸው ሰይሞላቸዋል፡፡

አቶ አውግቸው ተረፈ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሰረት በኪነ ጥበብ (ድርሰት) ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡

በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ

አቶ አጥናፍሰገድ ይልማ

አቶ አጥናፍ ሰገድ ይልማ በ1929 ዓም በአሩሲ ጠቅላይ ግዛት በጢቾ አውራጃ፣ በጢቾ ከተማ ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሩሲ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመጀመሪያ ደረጃ ትምርት ቤት፣ ሁለተኛውን ደግሞ በአዲስ አበባ ተምረዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ቢገቡም በወቅቱ በተፈጠረው ረብሻ ተባረው ሳይጨርሱት ቀርተዋል፡፡ በኋላም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በማታው መርሐ ግብር በፖለቲካ ሳይንስና በአስተዳደር በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም በሀገር ውስጥና በውጭ አጫጭር የጋዜጠኛነት ኮርሶችን ወስደዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የጋዜጠኛነት ሙያ መተዋወቅ ከጀመረበት ከ1950ዎቹ በኋላ ወደ መገናኛ ብዙኃን መጥተው ሞያውን ካስተዋወቁና ተጽዕኖ መፍጠር ከቻሉ ጥቂት ጋዜጠኞች አንዱ ናቸው፡፡

በ ‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ›፣ በ ‹አዲስ ዘመን›ና በ ‹ድምጽ› ጋዜጦች ላይ ኮርኳሪ የሆኑ መጣጥፎችን በመጻፍና ማኅበራዊ ሂስ በማቅረብ እንዲሁም ታሪክ አዘል ድርሳናትን በመከተብ የሚታወቁት አጥናፍ ሰገድ ይልማ በጻፏቸው መጣጥፎችና ባዘጋጇቸው ጋዜጦች ሰበብ በንጉሡም ሆነ በደርግ ሥርዓት ተመስግነዋል፤ ተቀጥተዋልም፡፡

ጋዜጠኛነት በዕውቀት የሚደገፍ፣ በእውነት የሚዘገብና ያለ አድልዎ የሚሠራ የተከበረ ሞያ እንደሆነ የሚያምኑትና በተግባርም ለመተርጎም የጣሩት አጥናፍ ሰገድ ይልማ በመጠሪያ ስማቸውና በብዕር ስማቸው ቁጥር ሥፍር የሌላቸውን መጣጥፎች ሠርተዋል፡፡ ወጣቶችም ለሞያው ዲሲፕሊን እንዲገዙ አድርገዋል፡፡ የታላላቅ ሰዎችን የሕይወት ልምድ ሕዝቡ እንዲካፈለው አመቻችተዋል፡፡ የነገሥታትንና የዐርበኞችን የተዳፈነ ታሪክ ሰነዶችን ፈትሸው በማውጣት አስነብበዋል፡፡

የደርግ ሥርዓት ካለፈ በኋላም በተመሠረቱ የግል ጋዜጦች ላይ አስተዋጽዋቸው የጎላ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ በኋላ ደግሞ በደራሲነት ስማቸው መጠራት ጀምሯል፡፡ ‹የበደል ካሣ› የሚል ልቦለድ፣ ‹የአቤቶ ኢያሱ አነሣስና አወዳደቅ›፣ እንዲሁም በቅርቡ ‹የሕይወቴ ምሥጢር› በሚል ርእስ ለ50ኛ የጋብቻ በዓላቸው ማስተዋሻ የሚሆን መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡

አቶ አጥናፍ ሰገድ ይልማ ልምዳቸውን ለማካፈል የማይሰስቱ፣ የወጣት ደራስያንን ሥራዎች በማርታት የሚተባበሩ፣ በየመድረኩ የአንጋፋ ጋዜጠኞችንና ደራስያንን ታሪኮች በመዘከር የሚያብራሩ፣ በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርን በልዩ ልዩ ኮሚቴዎች የሚገለግሉ፣ አንጋፋ ደራሲና ጋዜጠኛ ናቸው፡፡

አቶ አጥናፍ ሰገድ ይልማ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሰረት በሚዲያና ጋዜጠኛነት ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡  

በበጎ አድራጎት ዘርፍ

ዶክተር ቦጋለች ገብሬ

ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ በከንባታ ጠንባሮ ዞን ተወለዱ፡፡ በወቅቱ በአካባቢው ከ4ኛ ክፍል በላይ የተማረች ብቸኛዋ ሴት ነበሩ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ፣ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በእስራኤል ለመከታተል ነፃ የትምህርት እድል በማግኘታቸው በእስራኤል ሂብሩ ዩኒቨርሲቲ በፊዚዮሎጂ እና ማይክሮ ባዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በረዳት መምህርነት አገልግለዋል፡፡ ከዚያም ወደ አሜሪካ ተጉዘው በፓራሲቶሎጂ የድኅረ ምረቃ እና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከማሳቹስቴስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡

ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ አገራቸው ሲመለሱ የነበራቸውን 5000 (አምስት ሺህ) የአሜሪካ ዶላር ግብአት አድርገውና ከእህታቸው ጋር ተባብረው ኬ.ኤ.ም.ጂ የተሰኘውን ድርጅት እ.ኤ.አ በ1997 በከንባታ ጠንባሮ በአላባ ዞን አቋቋሙ፡፡ ድርጅቱ በወቅቱ በሰፊ ተዛምቶ የነበረውን የኤች.አይ.ቪ በሽታን መከላከል፣ የሴቶችን መጠቃት፣ የልጃገረዶችን ግርዛት፣ ጠለፋንና ሌሎችም ለሴቶች ጎጂ የሆኑ የባህል ተጽእኖዎችንና ልምዶችን የመግታት አላማ አንግቧል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኬ.ኤም.ጂ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች በ26 ወረዳዎች ውስጥ አገልግሎት እየሰጠና የተለያዩ መርሀግብሮችን በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ በቀጥታ ከ481 ሺህ በላይ፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግረና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች (ከዚህ መካከል 70% የሚሆኑት ሴቶች ናቸው) በመድረስ ላይ ይገኛል፡፡

የሴቶችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል እንደ ግርዛት፣ ጠለፋ፣ የቤት ውስጥ ጥቃት እንዲሁም ለጆሮ ያልደረሱ ኢሰብአዊ ድርጊቶችን መግታትና ሴቶች በክብር እንዲኖሩ ማድረግዓላማቸው ሆነ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ያላቸውን ጊዜ፣ ቁሳቁስ፣ እውቀት፣ ከሰው መግባባትና ህይወት የሰጣቸውን እድል ሁሉ ተጠቅመው በማህበረሰባቸው የለውጥ ምክንያት ለመሆን ተነሱ፡፡

ዶ/ር ቦጋለች እጅግ ብዙ የሆኑ ለራሳቸው ኩራትና እርካታ ለህብረተሰባቸውም አለኝታ የሚሆኑ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ እሳቸው የመሯቸው መርሃ ግብሮች በከንባታ የሚገኙ ሴቶች ለራሳቸው መብት እንዲቆሙ፣ ኑሯቸውን የሚመሩበት የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸውና በራሳቸው እንዲተማመኑ አስችሏቸዋል፡፡ በህብረተሰቡም ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ከነዚህም መካከል በከንባታ ጠንባሮ እ.ኤ.አ በ1999 100% የነበረ የሴቶች ግርዛት ስርጭት እ.ኤ.አ በ2008 በተደረገ ጥናት 3% ብቻ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይህን ተከትሎም ከግርዛት ጋር ተያይዞ ሴቶች በወሊድ ወቅት የሚደርስባቸው ስቃይና ሞት ቀንሷል፡፡ አስር ሚሊዮን ችግኞችንም በማስተከል የአካባቢው ሥነ ምህዳር እንዲሻሻል ጥረዋል፡፡

ዶ/ር ቦጋለች በማህበረሰቡ አስተሳሰብ ላይ በወንዶችም ጭምር ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ የማኅበረሰብ ውይይትን ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አጣጥመው በሁሉም የገጠር ክፍሎች ተግባራዊ ማድረጋቸው ይህ ለውጥ እንዲመጣ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በዚህ ምክንያትም እ.ኤ.አ በ2002 ዓ.ም ያልተገረዘች ሴት ባል ማግባት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ እናም ያልተገረዘች ሴት ባል ማግባት ችላለች፡፡

ዶ/ር ቦጋለች የእናቶችና ማህጸን ሆስፒታል ከንባታ ላይ እንዲሠራ፣ ሴት ተማሪዎች የሥራ እድል እንዲያገኙ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አይደፈሬ የነበረውን የጎጂ ባህል ተጽእኖ ሰብረው በማህበረሰብ ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ በኬ ኤም ጂ አማካይነት ያከናወኗቸው ሥራዎችና የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች በአገራችን ለወጡ አዳዲስ ህጎች በግብዓትነት ጠቅመዋል፡፡

ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሰረት በበጎ አድራጎት ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡

የበጎ ሰው ሽልማት የ 2008 ልዩ ተሸላሚ

ተስፋ ገብረስላሴ ዘብሔረ ቡልጋ

ለቤተሰባቸው ስምንተኛ ልጅ ናቸው፡፡ ልጅነታቸውም በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ያጌጠ ብቻ ሳይሆን ‹‹አስኳላ››ተብሎ ይጠራ በነበረው ዘመናዊ ትምህርት የታጀበ ነበር፡፡ ለግብረ ዲቁና የሚያበቃቸውን ትምህርት በተወለዱበት ቀዬ ከአጠናቀቁ በኋላ በ14 ዓመታቸው አዲስ አበባ የመጡት እኚህ በዛሬው ቀን ስማቸውን በአክብሮት የምንጠራው የዓመቱ በጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ፤ በአርበኛነታቸው፣ በደራሲነታቸውና በአሳታሚነታቸው ይታወቃሉ፡፡

በ1928 ዓ.ም. ፋሽስት ጣልያን ያወጀውን ጦርነት ይፋ ሲያደርግ፤ ‹‹ሀገሪቷ አትደፈርም፣ ባንዲራዋም እንዲረክስ አንፈቅድም›› ካሉ ወጣቶች መካከል ራሳቸውን መድበው አኩሪ ተጋድሎ ፈጽመዋል፡፡ በራሪ ወረቀት አሰናድተው የዓለም መንግሥታት ማኅበር ጦርነቱን አስመልክቶ ያሳየውን ቸልታ በብርቱ ተቃውመዋል፡፡ በወቅቱ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን ግፍ ለማኅበሩ ለማሳወቅ ወደ ጄኔቭ አምርተው ነበርና የእኝህ ሰው ተቃውሞና ነቀፌታ መወደድን አላተረፈም፡፡ ስለሆነም የሀገር ግዛት ሚኒስቴር እሳቸውንና ጽሑፋቸውን አሳድዶ ያዘ፡፡ ‹‹ባለን የጦር መሣሪያ እንዋጋ ብለህ ቅስቀሳ አካኺደሃል፤ ንጉሡን አዋርደሃል››ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው እኝህ አርበኛ፤ ኢትዮጵያዊ ወኔ ቀስቅሷቸው እንጂ በልቦናቸው ክፋት አድሮ እንዳልጻፉት ተናገሩ፡፡ ቀደም ሲልም ሌቦችና ጉቦኞች ከሥልጣናቸው መውረድ እንዳለባቸው የሚጠቁም ግጥም ጽፈው በማሠራጨታቸው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበርና፤ አሁንም ማንኛውም ጽሑፍ ለመንግሥት ሳያሳውቁና ሳያስፈቅዱ አሳትመው ቢያሠራጩ መንግሥታዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው በሚኒስትሩ በኩል ተናገራቸው፡፡

የጣልያን ጦር እየገፋ ሲመጣ ‹‹የኢትዮጵያ ፋና›› ብለው ለሚጠሩት በራሪ ዕትማቸው፤ ስለ ጠላት እንቅስቃሴ መረጃ ያስነብቡ ነበር፡፡ የሕይወት ታሪካቸውም እንደሚያስረዳው‹‹ሃገሪቱ ምንም ዓይነት ሚዲያ ባልነበራት በዚያ ወቅት የመንግሥትና የሕዝቡ አፈ ቀላጤ ብቸኛው ሰው›› ሆነው ነበር፡፡ ሕዝቡ እንዳይዘናጋና በጽንዓት ተጋድሎውን እንዲፈጽም እየጻፉ፣ የጻፉትን እያሳተሙ፣ ያሳተሙትን በነፃ እያሠራጩ ሳለ፤ ከቅርብ ሰዎቻቸው መካከል እንዱ የሚያደርጉትን ትግል ለጣልያን ጠቆመባቸው፡፡ ለጣልያን አድረው የነበሩ ሌሎች ግለሰቦችም፤ ተጠቋሚው ሰው ‹‹የተረገመ ነው፤ ሃገሩን የከዳ፣ ክብሩን ነጻነቱን አበሻን የጎዳ›› በሚል ግጥም አዋርዶናል፤ ብለው አቂመውባቸው ተከታተሏቸው፡፡ ማተሚያ ቤታቸውም ሊዘጋባቸው እንደሆነ ገመቱ፡፡ የተፈራው አልቀረም፤ ጣልያኖቹ ወደሳቸው መጡና አስረው ወሰዷቸው - ወደ አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ፡፡ ማተሚያ ቤቱ ሲፈተሸ ግን የተባሉት ጽሑፎች ሳይገኙ ቀሩ፡፡ እሳቸውም ‹‹የቅስቀሳ ጽሑፍ አልበተንኩም›› አሉ፡፡ ሆኖም ግን ለፍርድ ግራዚያኒ አደባባይ ቆሙ፡፡

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ጄነራል ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገ ሙከራ ሰበብ ጣልያን የበቀል እርምጃውን መውሰድ ሲጀምር እኝህ ባለ ታሪክ ‹‹ከሴረኞቹ ጋር የቀረበ ወዳጅነት አለህ›› ተብለው ይታደኑ ጀመር፡፡ በዚህ የተነሣ የኅትመት ሥራቸውን አቋርጠው፣ ቀስቃሽ ጽሑፎችን መበተን አቁመው፣ ከአርበኞች ጋር ተቀላቀሉ፡፡ ከባላምባራስ አበበ አረጋይ ጋር ተጋድሎአቸውን ያስመሰክሩ ጀመር፡፡ የጦር ስልት መንደፍ፣ አርበኛው ለአንድነቱ እንዲተጋ ማድረግ ሥራቸው ሆነ፡፡ የውስጥ አርበኞችን መዋቅር እንዲዘረጉ፣ የመረጃ ማቀነባበርና የማቀበል ሐላፊነትም እንዲረከቡ ሹማምንቱ ወሰኑ፡፡ የቀዘቀዘውን የአርበኞች ትግል ዳግም ለማነሣሣት በማኅበር ስም መንቀሳቀስ አዋጭ እንደሆነ ተረድተውም ‹‹የኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር››እንዲቋቋም ዓላማ ነደፉ፤ መዋቅሩን ዘረጉ፤ ተግባሩን አብራሩ፤ የማደራጀቱን ሥራ እነ ራስ አበበ አረጋይ ይዘው እውን አደረጉት፡፡

የውስጥ አርበኝነት ሥራቸውን እንዲሠሩም ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ ‹‹ከአርበኞቹ ጋር አልተስማማሁም›› ብለው ለአንድ የጣልያን አገልጋይ እጃቸውን ሰጡና ቃለ መሐላ ፈጽመው፤ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ያለውን የጣልያንን ጦር እንቅስቃሴና ጠቅላላ ሁኔታ መሰለል ቀጠሉ፡፡ በአርበኛነት ዘመናቸው የሦስት ልጆቻቸው እናት የሆኑት ወ/ሮ ቀለሟ ገብረ ወልድ በወረርሽኝ ሕመም መሞታቸውን ሰምተው ክፉኛ አዘኑ፡፡ ወ/ሮ ዓለሚቱ ንጉሤንም አግብተው ሁለተኛውን ትዳራቸውን መሠረቱ፡፡

ኢትዮጵያ የነጻነት ክብርዋ ሲመለስላት የኅትመት ሥራውን በአዲስ መንፈስ ተያያዙት፡፡ የማተሚያ መሣሪያዎቻቸው ተወርሰው ወደ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት እንዲዛወሩ ጣልያን አመቻችቶ የነበረ ሲሆን፤ ተስፋ ሳይቆርጡ ከግእዝ ወደ አማርኛ እየተረጎሙ፣ እያባዙ፣ የጸሎት መጻሕፍትን እያሠራጩ ከወረራው በፊት የነበረውን ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡

የነዮፍታሔ ንጉሤን፣ የነ ከበደ ሚካኤልንና የብላታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴን መጻሕፍት ከደራስያኑ እየተቀበሉ አትመው ማሠራጨታቸውን ቀጠሉ፡፡ ዘመናዊ የማተሚያ መሣሪያ (ማሽን) ከውጪ ሃገር አስመጥተው ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ትምህርት ነክ የሆኑ መጻሕፍትን በብዛት አትመው ለማሠራጨት ቆርጠው ተነሡ፡፡ ማተሚያ ቤቱን ተከሉ፡፡ የሕይወት ታሪካቸውን የያዘው መጽሐፍ እንደሚያስረዳው፤ ማተሚያ ቤቱ በኢትዮጵያ የኅትመት ኢንዱስትሪ ታሪክ በግሉ ዘርፍ የመጀመሪያውን ቦታ የያዘ ነው፡፡

ማተሚያ ቤቱ በግእዝና በአማርኛ የተጻፉ፤ የጸሎት፣ የድርሳናት፣ የተአምራት፣ የገድላት፣ የትርጓሜና የወንጌላት መጻሕፍትን አትሟል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ፣ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓትና፣ የሰዋስው ፅንሰ ሐሳብን፣ ልብ ወለድ ድርሰቶችን፣ የኢትዮጵያ ታሪክንና ሌሎችንም ጉዳዮች የሚያስተዋውቁ ከ 360 በላይ መጻሕፍትን አትመው አሠራጭተዋል፡፡ እኒህ የጥበብ ሰው ተርጉመዋል፣ አስተርጉመዋል፡፡ የልዑል መኮንን የሕይወት ታሪክ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የአመራር ጉዞ ጽፈዋል፡፡ ማተሚያ ቤቱ በስማቸው የሚጠራ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ 80 ሠራተኞችን ያስተዳድራል፡፡ ልጆቻቸውም ይኸው ማተሚያ ቤት ሥራው እንዲቀጥል ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል፡፡ በአርበኛነት ዘመናቸው ለፈጸሙት ጀብዱም የቀኝ አዝማችነት ማዕረግ ተቀብለዋል፡፡ በደርግ ዘመን በጽሑፎቻው የተነሣ ለመታሠር በቅተዋል፡፡

እኝህ በሃገር ፍቅር ቴአትር ቤት መሥራችነት፣ በአርበኛነት፣ ማተሚያ ቤት በመመሥረትና በአታሚነት የሚታወቁ፤ በግጥሞቻቸው ሀገር የመውደድን ትርጉም ይሰብኩ የነበሩት አባት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በ 97 ዓመታቸው ነው፡፡ የተወለዱት ግንቦት 26 ቀን 1892 ዓ.ም. ሰሜን ሸዋ፣ ቡልጋ ሲሆን፤ ብዙውን ጊዜ በየመጽሐፎቻቸው ቡልጋን ያነሧታል፡፡ የእሳቸው ሐሳብ ያረፈበት የፊደል ገበታ በየቤታችን ግድግዳ ተለጥፎ፣ በእጅም ተይዞ ተምረንበታል፡፡ የአማርኛ ሆሄ በያዘው በዚህ የፊደል ገበታም የሚከተለው ዓረፍተ ነገር ሠፍሮ ይገኝበታል፡፡ ‹‹ዕውቀት ይስፋ ድንቁርና ይጥፋ፤ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ፤›› ለእኝህ የተከበሩ አርበኛ፣ የብዕርና የኅትመት ባለሞያ፤ ‹‹የዓመቱ በጎ ሰው›› የተሰኘው የሽልማት ድርጅታችን ‹‹ልዩ ተሸላሚ›› ሲያደርጋቸው ታላቅ ደስታ ይሰማዋል፡፡

ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ !