የ2007 ተሸላሚዎች ዝርዝር

 

በቅርስና ባህል ዘርፍ

አቶ ሃብተስላሴ ታፈሰ

የተወለዱት በ1924 ዓም አካባቢ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነት አገኙ፡፡ ሥራ የጀመሩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የፕሬስና መረጃ ክፍል ኃላፊ ሆነው ነበር፡፡ አቶ ሀብተ ሥላሴ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትን እኤአ በ1961 ከመመሥረታቸው በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ቱሪስቶች እንደ ውጭ ሀገር እንግዶች ብቻ ይታዩ ነበር፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸው ከግምት አልገባም፡፡

እኚህ ሰው “የኢትዮጵያ ቱሪዝም አባት” ተብለው ይጠራሉ፡፡ የቱሪዝም ሥራ በአገራችን እንዲጀምር ከውጭ አገር ከቀሰሙት ልምድ በመነሳት በ1950ዎቹ መጀመሪያ ለአጼ ኃይለሥላሴ ሃሳብ ያቀረቡና ባገኙት ፈቃድም ለመጀመሪያ ጊዜ መሥሪያ ቤቱን አቋቁመው ሥራ ያስጀመሩ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡

የውጭ ሀገራት ዜጐች ሀገራችንን እንዲጐበኙ በተለያዩ አገራት እየተዘዋወሩ ቀስቅሰዋል፡፡ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የገበያ እድል ፈጥረዋል፡፡ ታሪካዊ ቦታዎችንና ባህላዊ አልባሳትን የለበሱ ኢትዮጵያውያን ፎቶዎች በፖስተርና በፖስት ካርድ በማሰራት አሁን ድረስ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው የቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡

በተለይም የአገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መለያ የሆነውን የ13 ወር የፀሐይ ብርሃን (13 months of sunshine) የሚለውን መርህ የፈጠሩና በሥራ ላይ ያዋሉ ናቸው፡፡ ዓለም ስለ ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲያውቅ፣ቱሪስቶችም ስለ ኢትዮጵያ በቂ መረጃ እንዲያገኙ፣ ዘመናዊ የቱሪዝም ሥራ እንዲያድግ ጠንክረው ሠርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅትን በማቋቋም ቱሪስቶች ባህላዊ መገለጫዎቻችንን እንደልብ እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡

እንዲሁም አሁን ያሉትን የሀገራችን የቱሪስት መስህብ የጉብኝት መስመሮች ማለትም፤ ወደ ጣና ሀይቅ፣ ጢስ አባይ፣ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ አክሱምና የመሳሰሉት ትኩረት እንዲያገኙ ትልቅ ጥረት ካደረጉት መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ 

ይህ ሥራቸው በንጉሡ ባለሟሎች ባለመወደዱ የውጭ አገር ቱሪስቶችን ለማስጐብኘት ወደ መርካቶ ሲወሰዱ “ገመናችንን ለዓለም ሊያሳይ ነው” ብለው ንጉሡ ዘንድ እስከመክሰስ ደርሰዋል፡፡ ከዚህ በባሰ የዘመኑ ሹማምንት የቱሪዝም መሥሪያ ቤቱን በጀት ስለከለከሉዋቸው በራሳቸው ገንዘብ እስከማስተዳደር፣ ቱሪስቶችንም በራሳቸው መኪና እስከመውሰድ የደረሱበት ጊዜ ነበር፡፡ 

ይህን ሁሉ መሰናከል በጥረታቸው አሳልፈው የቱሪዝም መሥሪያ ቤቱ በሁለት እግሩ እንዲቆም አብቅተዋል፡፡ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሲነሳ የእሳቸው ስም አብሮ ይወሳል፡፡  አቶ ሀብተሥላሴ የሀገር ባለውለታ፣ ላመኑበት ነገር እስከመጨረሻው በቁርጠኛነት ጥረት የሚያደርጉ፤ በህይወታቸው ኢትዮጵያን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ማየት የሚመኙ ናቸው፡፡

አቶ ሀብተ ሥላሴ የኢትዮጵያ ቱሪስት ድርጅትን በመመሥረት፣ በመላ ሀገሪቱና በመላ ዓለም ዞረው በማስተዋወቅ፣ ሀገራዊ የወግና የባህል ዕቃዎች ገበያ እንዲፈጠር በማድረግ ተግተዋል፡፡ ፎቶግራፎችን ራሳቸው በማንሣትና ጃፓን ድረስ ልከው በማሳጠብ የመጀመሪያዎቹን የቱሪዝም ፖስተሮች አዘጋጅተዋል፡፡ አሁን የ90 ዓመት አዛውንት ቢሆኑም ኢትዮጵያን ከማስተዋወቅ አልቦዘኑም፡፡

በማህበራዊ ጥናት ዘርፍ

አቶ ደሳለኝ ራህመቶ

በ1933 ዓም በናዝሬት ከተማ የተወለዱት ደሳለኝ ራሕመቶ የማኅበረሰብ ጥናት ባለሞያ ናቸው፡፡ በእርሻ ልማት፣ በድርቅና በእንደገና ሠፈራ ጥናቶችም ይታወቃሉ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአሜሪካ ኦሀዮ የአንጾኪያ ኮሌጅ በ1960 በፖለቲካ ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም በተነጻጻሪ ፖለቲካ (Comparative Politics)ከኖርዝ ኢስተርን ዩኒቨርሲቲ በ1963 ተቀብለዋል፡፡ 

አቶ ደሳለኝ ራሕመቶ ስማቸው ብዙ ጊዜ ተያይዞ የሚነሣው ከማኅበራዊ ጥናት መድረክ ጋር ነው፡፤ ማኅበራዊ ጥናት መድረክ እኤአ በ1988 የተመሠረተ መንግሥታዊ ያልሆነ የፖሊሲ የጥናት ተቋም ነው፡፡ አቶ ደሳለኝ እስከ 1988(እኤአ 2015) ድረስ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፡፤ በዚህ ጊዜም የማኅበራ ጥናት መድረክ በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ልዩ ልዩ ጥናቶችን የሚያደርግ፣ የፖሊሲ አማራጮችን የሚያቀርብና የኢትዮጵያን ማኅበራዊ ጉዳዮች በሚመለከት የሚጠቀስ ተቋም እንዲሆን አስችለውታል፡፡ 

ወደ ማኅበራ ጥናት መድረክ ከመምጣታቸው በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልማት ጉዳዮች ጥናት ተቋም( Institute of Development Research) መራሔ ጥናት በመሆን ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፤ ከዚህ ሥራቸው የተሰናበቱት እኤአ በ1997 የማኅበራዊ ጥናት መድረክን ለመመሥረትና በሁለት እግሩ ለማቆም ሲባል ነው፡፡ 

አቶ ደሳለኝ በግብርናና ገጠር ተኮር ጥናቶቻቸው የሚታወቁ ባለሞያ ናቸው፡፡ በዚህ ዘርፍም አያሌ ጥናታዊ ጽሑፎችንና መጻሕፍትን አሳትመዋል፡፡ አምስት መጻሕፍን በግላቸውና ከሌሎች ጋር በጋራ፣ ከ12 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን (Monographs)፣ ከ13 በላይ ሌሎች ጥናቶችንም(Articles in Journals) በጆርናሎች አሳትመዋል፡፡ ከስድስት በላይ በሚሆኑ መጻሕፍት ውስጥ ተካካይ ምዕራፎችን ጽፈዋል፡፡ 

አቶ ደሳለኝ የኢትዮጵያን ግብርናና የገጠር ሕይወት በተመለከተ ከመንግሥታዊ፣ መንግሥታዊ ካልሆኑና ከአካዳሚያዊ ተቋማት ጋር በጋራ አጥንተዋል፡፡ በዚህም ሥራቸው ‹በጥናትና ምርምር ላበረከቱት አስተዋጽዖ› የ1999(እኤአ) የልዑል ክላውድን ሽልማት ከኔዘርላንድ አግኝተዋል፡፡ 

አቶ ደሳለኝ ራሕመቶ በሞያቸው በሠሩት ጥናት በዚህች ሀገር ሊመጣ የሚችለውን አደጋ በዕውቀት ማስጠንቀቅ ከቻሉ ባለሞያዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በ1977 ዓም በኢትዮጵያድርቅ ተከስቶ በነበረ ጊዜ ባሳተሙት ‹ Agrarian Reform in Ethiopia› በሚለው ሥራቸው የ1967ቱ ሥር ነቀል የመሬት ይዞታ ለውጥ ያስከተላቸውን ችግሮች በዝርዝር ፊት ለፊት ለመግለጥ የቻሉ ባለሞያ ናቸው፡፡ 

በሳይንስ ዘርፍ

ፕሮፌሰር አበበ በጅጋ

ፕሮፌሰር አበበ በጅጋ የዓይን ሕመም ከፍተኛ ችግር በሆነበትና በቀላል ሕክምና ሊድኑ የሚችሉ የዓይን ሕመሞች ዓይነ ሥውርነትን በሚያስከትሉበት ሀገራችን ውስጥ ይህንን ችግር ለመፍታት በግንባር ቀደምነት ከተሰለፉ ባለሞያዎች መካከል ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና(MD,)ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በኦፕታልሞሎጂ ስፔሻላይዝድ ያደረጉት ፕሮፌሰር አበበ በጅጋ አውስትራልያ ከሚገኘው ኒው ካስል ዩኒቨርሲቲ በክሊኒካል ኤፒዲሞሎጂና ባዮ ስታትስቲክስ ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚሠሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ይህም አገልግሎታቸው ከ30 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ 

ፕሮፌሰር አበበ በጅጋ ሞያቸውን በተመለከተ በማስተማር፣ጥናት በማድረግና ልዩ ልዩ ሞያዊ ተቋማትን በማገልገል ይታወቃሉ፡፡ በሞያዊ ጆርናሎች አርታዒና አማካሪ በመሆን(ከአራት በላይ ቢሆኑ የኦፕቲሞሎጂ ጆርናሎች አባልና መሪ ተሳታፊ ናቸው)፣ በልዩ ልዩ ጉባኤያት አወያይና ተወያይ በመሆን(በሞያው ዘርፍ የተደረጉ ሁለት ሀገር አቀፍ ጉባኤያትን በመሪ ተወያይነት አገልግለዋል)፣ የሕክምና ማኅበራትን በመምራትና በቦርድ አባልነት በማገልገል(ከስድስት በላይ ሞያውን የተመለከቱ ማኅበራትና ሀገር አቀፍ ኮሚቴዎች ውስጥ በቦርድ አባልነትና በኮሚቴ አባልነት ያገለግላሉ)፡፡ 

እስካሁን ድረስ ኦፕቲሞሎጂን የተመለከቱ ከ30 በላይ ጥናቶችን በራሳቸውና ከአጋሮቻቸው ጋር ሆነው በመሥራት ያሳተሙ ሲሆን ላበረከቱት አስተዋጽዖም ልዩ ልዩ ሽልማቶችን ተቀብለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ኦፕቲሞሎጂካል ማኅበር (እኤአ በ2010) በጥናት መስክ ላበረከቱት አስተዋጽዖ የዕውቅና ሽልማት፣ እኤአ በ2012 በመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች የዓመቱ ምርጥ መምህር፣ እኤአ በ2014 የዓመቱ ምርጥ መምህር ተብለው ለስፔሻላይዜሽን በሚማሩ የክፍለ ትምህርቱ ተማሪዎች ተመርጠዋል፡፡ 

ዶክተር አበበ በጅጋ ከዚህ ሁሉ በላይ የሚታወቁት ዕውቀታቸውን ሳይሰስቱ ለመስጠት በሚያደርጉት ትጋትና ሕሙማኑን ለመርዳት በሚከፍሉት መሥዋዕትነት ነው፡፡ ከ1000 በላይ የሚሆኑ ሕጻናትን ከዓይነ ሥውርነት ታድገዋል፡፡ ተማሪዎቻቸው በዕውቀት ብቁ፣ በሥነ ምግባር ምስጉን፣ በሕዝብ አገልጋይነትም ታማኝ ሆነው እንዲወጡ ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዕውቀታቸውንም፣ ምክራቸውንም ይለግሳሉ፡፡ ተማሪዎችን በማክበር ሕዝብ የሚያከብሩ የሕክምና ባለሞያዎችን ለመፍጠር ይተጋሉ፡፡ በተደጋጋሚ በተማሪዎቻቸው ተመራጭ መምህር ያደረጋቸውም ይኼው ነው፡፡ ሕሙማኑን እስከመጨረሻው በመርዳት መፍትሔ እንዲያገኙ ይተጋሉ፡፡ ከእርሳቸው እጅ ሕክምናን ለማግኘት ዕድል ያገኙ ሁሉ ከሞያዊ ችሎታቸው ባሻገር የአባትነትና የወንድምነት ጠባያቸውን፣ ችግሩን ፈትተው የዓይን ብርሃንን ለመመለስና የዓይንን ጤንነት ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ግብግብ ያስታውሳሉ፡፡ የሞያ አጋሮቻቸውና ተማሪዎቻቸው ‹ችግርን በመፍታት እንጂ ገንዘብን በማግኘት የማይደሰቱ› ይሏቸዋል፡፡ 

በኪነ-ጥበብ ዘርፍ

ሰዓሊ ታደሰ መስፍን

ሰዓሊ ታደሰ መስፍን በ1945 ዓ.ም በወልዲያ ነበር የተወለደው፡፡ ከእረኝነቱ ጀምሮ እጅና እግሩ ላይ በእንጨት በመሞንጨር ሥዕልን የጀመረው አዳጊው ምንም እንኳን ዝንባሌው ወደ ሥዕል ማጋደሉን ከልጅነቱ ቢረዳም መደበኛ ትምህርቱን ከመከታተል ወደ ኋላ አላለም፤ በዚሁ መሠረት በዕቴጌ ጣይቱ ብጡል ት/ቤት መደበኛ ትምህርቱን ጀምሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ቆይታውን እንዳጠናቀቀ የ6 ዓመቱ ታዳጊ ከአጎቱ ጋር ለመኖር ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላም በስዊዲሽ ሚሽን ት/ቤት ገብቶ መደበኛ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በበዕደ ማርያም ት/ቤት አጠናቀቀ፡፡ ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን ግን በትምህርት ቤቱ ውስጥ ለሚዘጋጀው መጽሔት “ኢሉስትሬሽን” የውጭ ሽፋን የመሳሰሉትን ይሰራ ነበር፡፡

ሰዓሊ የመሆን ጥልቅ ፍላጎትና ችሎታ ስለነበረው 1960 ዓ.ም ሥነ ጥበብ ት/ቤት ገባ፡፡ በአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ት/ቤት ቆይታው ታዋቂው ሰዓሊ ገ/ክርስቶስ ደስታ ያስተማረው ሲሆን እንደነ ዲዛይነር ታደሰ ግዛውን ጨምሮ በድንቅ መምህራን መማሩን የሚናገረው ሰዓሊ ታደሰ በተማሪነቱ ከሌሎች አቻዎቹ የላቀ ሥራ በመሥራት የከፍተኛ ትምህርቱን በማዕረግ አጠናቋል፡፡ የዛሬው አንጋፋው የያኔው ወጣቱ ሰዓሊ ከተመረቀ ከአምስት ዓመት በኋላ የብሔራዊ ቴአትር “አንድ ሰዓሊ መርጣችሁ ላኩልን” በማለት ለሥነ ጥበብ ት/ቤቱ በደብዳቤ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ሰዓሊ ገ/ክርስቶስ ደስታም በወጣቱ ችሎታ በመተማመን ሰዓሊ ታደሰን ወደ ብሔራዊ ቴአትር ላከው፡፡ በመድረክ ዲዛይን ሥራው የብዙዎችን አድናቆት የተቸረው ሲሆን በቅርበት ሥራውን የተከታተሉ ሙያተኞች “በዚያን ዘመን እሱ ይሰራቸው የነበሩት የመድረክ ዲዛይኖች ዛሬ እንኳ በዲጂታል ዘመን እንዳልተሠራ ይመሰክራሉ፡፡

ለተጨማሪ ከፍተኛ ትምሕርት ወደ ራሽያ ሀገር በማቅናት በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ በሚገኘው ሬፒን አካዳሚ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን ለመከታተል የቻለ ሲሆን በዚህ ተቋም በነበረው ቆይታ ከራሽያ ተማሪዎችም ሆነ ከሌላ ሐገር ከሄዱት ተማሪዎች እጅግ የላቀ ብቃት አሳይቷል፡፡ በዚህም ልዩ ብቃቱ በአካዳሚው ታሪክ የመጀመሪያው የውጭ አገር ዜጋ የክብር ተሸላሚ በመሆን ማስተርሱን ይዞ ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡ በከፍተኛ ውጤት በማዕረግ ተመርቆ ሐገሩ ከተመለሰ በኋላ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ስር የሚገኘውን እና ለሀገራችን ፋና ወጊ የሆነውን የአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ት/ቤት ሰዓሊ ታደሰን እና ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህን ተቀብሎ በተቋሙ የነበረውን የኪነ ንድፍ(ድሮዊንግ) ደረጃ በጣም ከፍ ያደረጉበት ጊዜ ነበር፡፡

በደርግ ጊዜ በየጊዜው ለብሔራዊ ግዴታ በሚሉ እና በሌሎችም መነሻዎች ምንም ሳይከፈለው በነፃ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፖስተሮችንና ሥዕሎችን በመስራት፣ የሶሻሊስት ኢትዮጵያ ዓርማን በመቅረፅ፣ ለታላቁ የሕዝብ ለሕዝብ ትዕይንት የሚሆኑ የመድረክ እና የአልባሳት ዲዛይን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በማዘጋጀት፣ እንዲሁም የሀገራችን የመገበያያ ሳንቲሞች (25 ሳንቲም እና 50 ሳንቲም) ላይ የራሱን ሙያዊ አስተዋፅዖ በማድረግ አንጋፋው አስተማሪ እና ሰዓሊ ታደሰ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ግዴታ ሊወጣ ችሏል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በመንግሥት እና በሌሎችም አካላት ሙያዊ አስተዋጽዖን ሲጠየቅ ወደ ኋላ ብሎ የማያውቀው ሰዓሊው ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላም በተለያዩ የመታሰቢያ ሥራዎች ላይ ሙያዊ ተሳትፎን አድርጓል ከቅርብ ጊዜ ሥራዎቹ ውስጥም ትግራይ ላይ ያለውን የሰማዕታት ሐውልት የመጀመሪያውን ንድፍ ያጠናና የፈጠረ እንዲሁም በአማራ የሰማዕታት ሐውልት ሥራ ላይ የበዛ አስተዋፅኦ ያደረገባቸውን መጥቀሱ በቂ ይሆናል፡፡

ሰዓሊ ታደሰ መስፍን ገና በወጣትነቱ ከሥነ ጥበብ ት/ቤቱ በማዕረግ ሲያጠናቅቅ ጃንሆይ የወርቅ ሰዓት ሸልመውታል፡፡ የሥነ ጥበብ እና የመገናኛ ብዙኃን ሽልማት ላይ በምርጥ ሰዓሊነቱ መሸለሙ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ለበርካታ ዓመታት ሀገሩን ያገለገለው አንጋፋው ሰዓሊ የሚገባውን ያህል ቀርቶ ለሥራው መታሰቢያ የሚሆን እውቅናን እንኳን በተለይ ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቱ አልተሰጠውም፡፡ ከተቋሙ በተቃራኒው ግን በሥነ ጥበብ ት/ቤቱ ተማሪዎቹ በተደጋጋሚ ሊሸለምና ሊመሰገን ችሏል፡፡ 

በአሁኑ አጠራሩ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ጥሩ ጥሩ መምህራን ቢኖሩም ለተማሪዎች የምንጊዜም ምርጥ መምህራቸው በመሆን ሰዓሊ ታደለ መስፍን በእነርሱ የቃል ምስጋና ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡  “ተማሪ በአንድ ድምፅ የሚወደውና የሚያደንቀው አንጋፋ ሰዓሊ ነው” በማለት የሚመሰክሩለት ተማሪዎቹ “ለመምህራቸው እና እውቁ ሰዓሊ ታደሰ መስፍን የማይገባው ሽልማት የለም” ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ታዋቂው ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ በበኩሉ  “በሥነ ሥዕል እንደ ታደሰ መስፍን ለመንግሥት ሆነ ለአገሩ በሚገባ ያገለገለ ሰው የለም፡፡ እሱ እንደዚህ አድርግ ካሉት “እምቢ” የማይል ሰው ነው፡፡ በዚያ ላይ ቢያንስ እንኳን መልሳችሁ እንደዚህ አድርጉልኝ የማይል ነው፡፡” በማለት የአንጋፋውን ሰዓሊ ብቃት ይመሰክራል፡፡ 

አንጋፋው ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ በበኩላቸው “እንደ ታደሰ መስፍን ዓይነት ሠዓሊ በዘመናት ውስጥ አንድ ሁለት ሰው ነው የሚታየው” በማለት አድናቆታቸውን ካወሱ በኋላ የታደሰ ብቃትን የሚያህል የዕውቀትና የጥበብ ሰው የሌለን በመሆኑ ከእኛም አልፎ አፍሪካን የሚያስጠራ ነው፡፡ በማለት ስለሙያተኛው ብቃት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

በበጎ አድራጎት ዘርፍ

ወ/ሮ ትርሃስ መዝገበ

በአሥመራ ከተማ ተወልዳ ያደገችው ትርሐስ መዝገበ ወደ ከተወሰኑ ቤተሰቦቿ ጋር የሃያ ዓመት ልጅ ስትሆን ወደ አዲስ አበባ መጣች፡፤ ያን ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቅቃ ነበር፡፡ ወደ ጣልያን ለመሄድ ቪዛ እየጠበቀች እያለች እስከዚያው ጊዜዋን በሥራ ለማሳለፍ ሳሊኒ የተባለው የጣልያን የኮንስትራክሽን ድርጅት ይሠራ ወደነበረበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሄዳ ፓዌ ከተማ በአንድ ሱፐር ማርኬት ውስጥ ተቀጠረች፡፡ በጥቂት ጊዜ ውስጥም የሱፐር ማርኬቱ ሥራ አስኪያጅ ሆነች፡፡ 

በዚህ ጊዜ በአካባቢዋ የሚገኙ ሕዝቦችን ለማየትና ለማጥናት፣ ስለ ኑሯቸውም ለመረዳት ዕድል አግኝታለች፡፡ በመካከሉም የቪዛዋን ጉዳይ ለመከታተል ወደ አዲስ አበባ ስትመጣ በአንዳንድ ጉዳዮች ከቤተሰቦቿ ጋር አልተግባባችም፡፡ ይህም የጣልያኑን ጉዞ ርግፍ አድርጋ ትታ ለጣልያን ጉዞ የሰበሰበቺውን ገንዘብ ይዛ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዳግም እንድታመራ አደረጋት፡፡ 

በ1987 ዓም አንድ ቀን ከጓደኛዋ ጋር በመኪና በጫካ ውስጥ ሲጓዙ የአንዲት ሴት የጩኸት ድምጽ ሰሙ፡፡ ምን እንደሆነ ለማወቅ ወደ ጫካው ሲገቡ ያየቺው ነገር የሕይወቷን መሥመር ቀየረው፡፡ አንዲት እናት ልጇን በወሊድ በማጣቷ የተነሣ ራሷን ዛፍ ላይ ሰቅላለች፡፡ ይህ ለምን ሊሆን ቻለ? የሚለው ለትርሐስ ትልቅ ጥያቄ ነበር፡፡ 

በጉሙዝ ባሕል የሴት ልጅ ደም ርኩስ ነው፡፡ ማንኛዋም ደም የሚፈሳት ሴት ከሰው መገለል አለባት፡፡ አንዲት ሴት ልትወልድ ምጧ ከመጣ ከቤት ወጥታ ከሰውም ተለይታ ብቻዋን ወደ ጫካ ትላካለች፡፤ እዚያም ብቻዋን አምጣ፣ ብቻዋን ተገላግላ ብቻዋን መውለድ ይጠበቅባታል፡፡ ይኼ ነገር ትርሐስን አስደነገጣት፡፤ የጉሙዝ ሴቶችንም መከራ አሰበች፡፡ ከዚህ በኋላም ይህንን ልማድ ልትታገለው ቆረጠች፡፡ 

ወደየመንደሩ እየገባች ከጉሙዞች ጋር አወራች፣ ባሕላቸውንና አኗኗራቸው ተረዳች፣ ችግራቸውን ተገነዘበች፣ እርሷ የት ጋ ብትሠራ ለውጥ እንደምታመጣም ዐወቀች፡፤ ከዚህ በኋላም ‹ሙጁጄክዋሎካ› የተሰኘ ድርጅት በ1990 ዓም መሠረተች፡፡ ይህንን በሴቶች ችግር ላይ የሚሠራና ችግራቸው ለመፍታት የሚተጋ ድርጅት በመምራትና ከጉሙዝ ሴቶች ጋር በመሥራትም ከ24 ዓመታት በላይ በክልሉ ኖራለች፡፡ 

ትርሐስ ዋና ዓላማዋ የጉሙዝ ሴቶች ጫካ ውስጥ ሳይሆን ቤት ውስጥ እንዲወልዱ ማሳመን ነበር፡፡ በጉሙዝ ባሕል አምላክ የሴት ደም ይፈራል፡፡ ለዚህ ነው ሴቷ ወደ ጫካ የምትሄደው፡፡ ትርሐስ ደግሞ ሕዝቡ የሚፈልገው በማሟላት ሴቶች ቤት ውስጥ እንዲወልዱ ለማሳመን ትተጋለች፡፡ ለዚህ ነበር ‹የትርሐስ አምላክ ደም አይፈራም› ያሏት፡፡ 

ትርሐስ የጉሙዝ ወንዶችንና ሴቶችን በማሳመንና በአካባቢያቸው የሚገጥማቸው ችግር በመፍታት ሴቶች ጫካ ውስጥ ሳይሆን በክብር ቤታቸው እንዲወልዱ፣ የሕጻናት ሞት በከፍተኛ ሁኔታ በአካባው እንዲቀንስ፣ የእናቶችም ችግር ትርጉም ባለው መልኩ እንዲፈታ ለማድረግ የቻለች ብርቱ ሴት ናት፡፡ ከሕዝቡ ጋር ኖራ፣ ሕዝቡንም ተረድታ፣ ችግሩን አብራ የፈታች ጀግና፡፡ 

በቢዝነስና ስራ ፈጠራ ዘርፍ

ሰላም ባልትና

ሰላም ባልትና የቤተሰብ ኩባንያ ነው፡፡ የቤተሰቡ እናት በባሕላዊ መልኩ ጉልት ላይ የባልትና ሥራዎችንና ቅመሞችን እየሸጡ ይተዳደሩ ነበር፡፡ የእርሳቸው ዐቅም ሲዳከም ወንዶች ልጆቻቸው የእርሳቸውን ሞያ መከተል ጀመሩ፡፡ ይበልጥም ሥራውን ለማስፋፋት 300 ብር ተበድረው ሥራን ለማጠናከር ሞከሩ፡፡ 

በ1991 ዓም ወንድማማቾቹ ራሳቸው ዕቃ እየገዙ፣ የባልትና ውጤቶችንም እያዘጋጁ፣ በሱቅም ተገኝተው እየሸጡ ሥራውን በዘመናዊ መልክ መሥራት ጀመሩ፡፡ የደንበኞችን ትኩረት ለመሳብና ሥራውን ዘመናዊ መል ለማስያዝ የባልትና ውጤቶችን እያሸጉ መሸጥ ጀመሩ፡፡ 

በመጀመሪያው የሥራ ዘመን ደንበኞች የታሸጉ የባልትና ምርቶችን ለመግዛት ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ በወቅቱ ከበርበሬና ሽሮ ጋር ባዕድ ነገሮች እየተቀላቀሉ እየተሸጡ በሚዲያ ይቀርቡ ስለነበር ደንበኞች የታሸጉ የባልትና ውጤቶችን ለመግዛት ጥርጣሬ ነበራቸው፡፡ ቀስ በቀስ ግን ደንበኞችን በማሳመንና ያለማሰለስ በመሥራት ‹ሰላም ባልትና› የሚለው የባልትና ስም የጥራት ምልክት እንዲሆን አስችለዋል፡፡ 

ሰላም ባልትና ባሕላዊ የባልትና ምርቶችን በዘመናዊ መል ለገበያ በማቅረብ ሰዎች ጊዜ ከሚጠይቀው የሀገራችን የባልትና ሥራ በጊዜ እጥረት ምክንያት እንዳይለያዩ፣ የባልትና ምርቶችም በቀላሉ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ፣ በውጭ ሀገር የሚኖረው ዜጋ በቀላሉ እንዲያገኛቸው ለማድረግ አስችሏል፡፡ ሰላም ባልትና ከ300 ተነሥቶ ዛሬ ራሱን የቻለ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሲሆን በሥሩም ከ200 በላይ ሠራተኞችን ያስተዳድራል፡፡ ለምርቱ ማዘጋጃና ማቀነባበሪያ የሚሆኑ ተቋማትንም አደራጅቷል፡፡ የምርቶቹን ንጽሕና ለማረጋገጥ ለሠራተኞቹ ተገቢውን የጤና ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ 

ሰላም ባልትና ለተለያዩ ድርጅቶች ምርቶቹን በመለገሥ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ይጥራል፡፡ ለአበበች ጎበና የርዳታ ድርጅት፣ ለሜሪ ጆይ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኙ ማየት ለተሣናቸው ተማሪዎች፣ ለሴት ደራስያን ማኅበር፣ ለአካባቢ ማኅበረሰብ ዐቀፍ ፖሊስ በየጊዜው ርዳታ ሰጥቷል፡፡ በቂርቆስ አካባቢ ለሚገኙ ወጣቶችም የስፖርት ትጥቆችን አበርክቷል፡፡ 

በስፖርት ዘርፍ

ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ

ጥር 1939 ዓ ም ሰሜን ሸዋ ተጉለት እና ቡልጋ የተወለዱት ወልደ መስቀል ኮስትሬ በ2 ዙር በመጀመሪያ ከ1964 -1970 እንደገና ደግሞ ከ1974 -1982 በአጠቃላይ 14 አመታትን በወጣትነታቸው ካሳለፉባት የምስራቅ አውሮፓዋ ሀገር ሀንጋሪ በባዮሎጂ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪ ባለቤት ናቸው፡፡ 

ዶ/ር ወልደመስቀል ወደ ሀንጋሪ ለትምህርት ከማምራታቸው ከሳምንታት በፊት በ1964 በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለሚሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድናችን በ800 ሜ እና 1500 ሜትር ለተወዳዳሪነት ተመርጠው ነበር፡፡ ነገር ግን ትምህርት ይሻለኛል በማለት ውድድሩን በመተው ወደ ሀንጋሪ አምርተዋል፡፡ የአትሌቲክስ አሰልጣኝነትን የጀመሩት በኮተቤ ኮሌጅ አስተማሪ እያሉ በ70ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲሆን በ1972 የሙኒክ ኦሎምፒክ በሚሳተፈው ቡድናችን ውስጥ ዋና አሰልጣኝ ለነበሩት ንጉሴ ሮባ ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ነበር፡፡ 

ዶክተር ወልደመስቀል በ1982 የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በስፖርት ኮሚሽን ውስጥ በከፍተኛ ባለሙያነት ሰርተዋል፡፡  ወደ አትሌቲክስ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝነት የመጡት የአሰልጣኝ ንጉሴ ሮባን ኅልፈት ተከትሎ በ1992 ነው፡፡ 

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተቻቸው ምርጥ ምርጥ አትሌቶች ጀርባ እኝህ ኮስታራ አሰልጣኝ ይገኛሉ፡፡ ከ1992 የባርሴሎና እስከ 2008 ቤጂንግ ኦሎምፒክ ለ16 ዓመታት በዘለቀው የዋና አሰልጣኝነት ዘመናቸው ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ያኮሯትን የ5000 እና የ10,000 ሜትር አትሌቶች ለውጤት በማብቃት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 

ዶ/ር ወልደመስቀል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንን እያሰለጠኑ በተሳተፉባቸው አምስት ኦሎምፒኮች ላይ 28 ሜዳሊያዎችን በድምሩ ለሀገራቸው አስገኝተዋል (13 ወርቅ 5የብር እና 10 የነሐስ ሜዳሊያዎችን)፡፡ በአትሌቲክሱ ዓለም ለአሰልጣኞች የሚሸለመውን የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝነት ሽልማትን በ2006 ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ብሎ ሸልሟቸዋል፡፡ 

በጋዜጠኝነትና ሚዲያ ዘርፍ

አቶ ያዕቆብ ወልደማርያም

አቶ ያዕቆብ ወልደ ማርያም የኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የእንግሊዝኛ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ለ56 ዓመታት ያለማቋረጥ በመሥራት ይታወቃሉ:: አሁንም በእንግሊዝኛው የሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በኤዲተርነት በመሥራት ላይ ይገኛሉ:: 

እርሳቸው የዛሬ 56 ዓመት በኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ሲቀጠሩ ደሞዛቸው 300 ብር አይደርስም ነበር፡፡ በጊዜው ሄራልድን ሲቀላቀሉ 30 አመት የሞላቸው አቶ ያዕቆብ በዓመቱ በ1952 የሄራልድ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ ለመሆን ችለዋል፡፡ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን በበላይነት የሚመሩት አቶ ዓምደ ሚካኤል ደሳለኝ ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ እንዲሠራ ይመኙ ስለነበር አቶ ያዕቆብ በሄራልድ ዐቅማቸውን እንዲያወጡ ዕድል ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ርእሰ አንቀጽና መጣጥፎችን በመጻፍ ችሎታቸውን ያሳዩት አቶ ያዕቆብ ጥረታቸውን በማጠናከር ቀጠሉበት፡፡ ያኔ እርሳቸው ዋና አዘጋጅ ከመሆናቸው አስቀድሞ ዶክተር ዴቪድ ታልቦት የሄራልድ ዋና አዘጋጅ ነበሩ፡፡ 

አቶ ያዕቆብ በሄራልድ በሠሩበት ዓመት ጠንካራ አገራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ሙያዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል ነዋሪዎች ገንዘብ ቆጥበው የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል ሲሉ በርእሰ አንቀጻቸው ሙግት ገጥመዋል፡፡ ያን ጊዜ ለንጉሡ ቀረቤታ ያላቸው ብቻ ቤት ያገኙ ስለነበር ደሃውም የቤት ባለቤት ይሁን ሲሉ አቶ ያእቆብ በርእስ አንቀጻቸው ላይ አስፈረዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ሠራተኛው የጡረታ መብቱ ሊከበርለት ይገባል ሲሉ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል፡፡ 

ከሄራልድ ከለቀቁ በኋላ በመነን መጽሔት፤ በቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ፤ በአዲስ ሪፖርተር በኤዲተርነት የሠሩ ሲሆን በሚሠሩትም ሥራ ደስተኛ ነበሩ፡፡ በንጉሡ ዘመን ለ15 ዓመታት፤ በደርግ ዘመን ለ17 ዓመታት፤ ከዚያ በኋላ ላለፉት 24 ዓመታት በጠቅላላ ለ56 ዓመታት በሙያቸው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ አቶ ያዕቆብ ከ1983 በኋላ ዘሰን፤ ዘሪፖርተር፤ ፎከስ ለተሰኙ የኅትመት ውጤቶች ሠርተዋል፡፡ በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ማሳተም ለሚፈልጉ ሰዎችም ሙያዊ ምክር በመስጠት ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ 

አቶ ያዕቆብ ሄራልድ ከመግባታቸው በፊት አምኃ ደስታ ትምህርት ቤት የሳይንስ መምህር ሳሉ የትምህርት ቤት ጋዜጣ እንዲጀመር አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አቶ ያዕቆብ አልፎ አልፎ የጋዜጠኝነት ኮርስ ከመውሰዳቸው ሌላ በመደበኛነት ጋዜጠኝነትን አልተማሩም፡፡ ይልቁንም በእንግሊዝ ስኩል ኦፍ ለንደን  ምሕንድስናን ለተወሰነ ዓመት አጥንተዋል፡፡ በለንደን እያሉ ጋዜጦችን በማንበብ ራሳቸውን በራሳቸው ጋዜጠኝነት ማስተማር ችለዋል፡፡ አቶ ያዕቆብ የራሳቸውን ግለ ታሪክ በ1995 ያሳተሙ ሲሆን አሁን ዕድሜያቸው 86 አልፎአል፡፡ አንድ ዓይናቸው ማየት ያቆመው አቶ ያዕቆብ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ናቸው፡፡ የትውልድ ቦታቸውም ወለጋ ነቀምት ሲሆን  አዲስ አበባ መጥተው በኮተቤ ተምረዋል፡፡ 

ለአገራችን የእንግሊዘኛ ጋዜጦችና መጽሔቶች እድገት ከወጣትነት እስከ አረጋዊነት እድሜያቸው ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አስተዋጽኦ ያደረጉትና እያደረጉ ያሉት እኚህ አንጋፋ ጋዜጠኛ  አሁንም ደከመኝ ሳይሉ ጠንክረው እየሰሩ ነው፡፡

መንግስታዊ ሃላፊነትን በብቃት በመወጣት ዘርፍ

አቶ ሽመልስ አዱኛ

አቶ ሽመልስ አዱኛ በበርካታ የመንግሥትና የእርዳታ ድርጅቶች በኃላፊነት ሰርተዋል፡፡ አቶ ሽመልስ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አማካሪ ሆነው ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከመንግሥት ኃላፊነታቸው በተጨማሪ በግላቸው በድርቅ እና በኅብረተሰብ አሰፋፈር ጉዳዮች ላይ ለግል ድርጅቶችና ለመንግሥት አማካሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ አቶ ሽመልስ በበርካታ ሰብአዊ ሥራዎች ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ 

አቶ ሽመልስ አዱኛ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርን የተቀላቀሉት በመንግሥት ሥራ ውስጥ ለረጅም ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ነው፡፡ አቶ ሽመልስ በሕንድ አገር ስለ ማኅበረሰብ አገልግሎት ከተማሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የበርካቶችን ሕይወት የቀየረ የሰብአዊነት ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡ አቶ ሽመልስ አዱኛ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው የተሸሙት ከዚህ በኋላ ነው፡፡ 

አቶ ሽመልስ አዱኛ የእርዳታና መልሶ ማቋቋም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ሲሰሩ በ1977 ዓ.ም ድርቅ የተጎዱ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት የሚታደግ ሥራ ሠርተዋል፡፡ የዚህ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው በሠሩበት ወቅት በድርቁ የተጎዱ ወገኖችን ሊረዱ የሚችሉ ዓለም አቀፍ ለጋሾችንና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርን ለማስተባበር ብዙ ደክመዋል፡፡ 

አቶ ሽመልስ አዱኛ በ1993 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዘዳንት ሆነው ተሸመዋል፡፡ በፕሬዘዳንትነት በቆዩባቸው ስምንት ዓመታት ውስጥ ማኅበሩ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ወቅት ፈጣን የሰብአዊነት ሥራዎችን እንዲሰራ አስችለውታል፡፡ 

አቶ ሽመልስ አዱኛ እ.ኤ.አ ከ2000 ጀምሮ በአፍሪካ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዘዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ አቶ ሽመልስ አዱኛ በአፍሪካ የሥራ ፈጠራ አምባሳደር፣ የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥራ ፈጠራና ድኅነት ቅነሳ ፐሮገራም የኢትዮጵያ አስተባባሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ 

አቶ ሽመልስ አዱኛ በግል ትጋታቸው፣ የሰብአዊነት ሥራ እንዲበረታታ ባደረጉት አስተዋጽዎና የሰብአዊነት መርሆዎች እንዲታወቁ በሠሯቸው ሥራዎች እ.ኤ.አ በ2011 ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ማኅበር የሔነሪ ዱና ሜዳልያ ተሸልመዋል፡፡ 

የ2007 ዓም የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ ተሸላሚ

ፊታውራሪ ዐመዴ ለማ

የወሎ ጠቅላይ ግዛት ይባል በነበረው ግዛት፣ ወረሂመኑ ተብሎ በሚጠራው አውራጃ፣ መጋቢት 1913 ዓም ተወለዱ፡፡ አባታቸው በልጅነታቸው በሞት ስለተለዩዋቸው ኑሮ ከበዳቸውና ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር ዕንቁላልና ሌሎች ነገሮችንም መነገድ ጀመሩ፡፡ ደሴ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በማታው መርሐ ግብር እስከ ስድስተኛ ተማሩ፡፡ በ1936 ዓም ደግሞ ወ/ሮ ዘምዘም  ኢብራሂምን አገቡ፡፡ ከእኒህ ወይዘሮ ጋርም ለስድሳ ዓመታት በጋብቻ ኖረዋል፡፡ 

ፊታውራሪ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በወቅቱ ከነበሩ ነጋዴዎች ልምድ ቀሰሙ፡፡ ይህንን ልምድ ተጠቅመውም ነግደው የሚያተርፉ፣አትርፈውም ለሌሎች የሚተርፉ ነጋዴ ሆኑ፡፡ 

ፊታውራሪ በሕዝብ ዘንድ ይበልጥ ያሳወቃቸውና ያስወደዳቸው ለሰው ልጅ ያላቸው ክብርና፣ ለሰውነት የሚሰጡት ዋጋ ነው፡፡ ይህም ለፓርላማ አስመርጧቸው በ1948 ፓርላማውን ሲቀላቀሉ ፓርላማው ከፍተኛ መሻሻል ያሳየበት ዘመን ሆነ፡፡ ለዚህም እነ ፊታውራሪ ዐመዴ ለማና ሌሎች ያደረጉት አስተዋጽዖ ወሳኝ ነበር፡፡ በኃላፊነት ዘመናቸው ኢትዮጵያ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች መብታቸው እኩል ተከብሮ በመፈቃቀርና በመከባበር የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ተግተዋል፡፡ አንዳንድ በዓላት ቀርተው የሙስሊም በዓላት እንዲተኩባቸውም ጥረት አድርገዋል፡፡ 

በፍትሕ ሥርዓቱ የነበረው ፍርደ ገምድልነት ቀርቶ የተሻለ የፍርድ ሥርዓት እንዲኖር እርሳቸውና ስድስት ሌሎች የፓርላማ አባላት ያቀርቡ በነበረው ሐሳብና ትችት የተነሣ በንጉሡ ዘንድ ቅያሜ አስከትለው ከደረጃ ዝቅ ብለው እንዲሠሩ ተደርገው ነበር፡፡ ከፓርላማ እንዲወጡም ሤራ ተጎንጉኖባቸው ነበር፡፡ በፓርላማ አባልነታቸው ካነሡዋቸው ሐሳቦች መካከል የአክሱም ሐውልት መመለስ፣ የመሬት ይዞታ መሻሻልና የጤና ግብርን የተመለከቱት ይጠቀሱላቸዋል፡፡ 

ፊታውራሪ ዐመዴ በሕይወት ዘመናቸው ከሚደሰቱበት ሥራቸው መካከል የአክሱምን ሐውልት ለማስመለስ በተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ውስጥ ያደረጉት አስተዋጽዖ ለስኬት መብቃቱ ነው፡፡ ፊታውራሪ ዐመዴ የሀገራቸውን ጉዳይ ከምንም ጉዳይ በላይ የሚያስቀድሙ ናቸው፡፡ ለእርሳቸው ጉዳዩ የክርስቲያን ሆነ የሙስሊም አንድ ነው፡፡ መስጊድ ያሠሩትን ያህል ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል፡፡ ‹በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች› የሚለው ባዕድነት የሚያመጣ ስያሜ እንዲቀር የታገሉትን ያህል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚገኙ አባቶች መለያየታቸውን ባለመደገፍ ሁለቱንም አባቶች ቀርበው ይቆጡ፣ ይገሥፁና ‹‹ይህቺ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን የእናንተ ብቻ አይደለችም›› እያሉ ይናገሯቸው ነበር፡፡ በ1997 ዓም የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ የታሠሩትን የቅንጅት አመራሮች ለማስፈታት በተደረገው የሽምግልና ጥረትም ከሌሎች ወገኖች ጋር በመሆን ከላይ ታች ደክመዋል፡፡

ከዚህ ተግባራቸው ባሻገር የውኃ ዋና ፌዴሬሽን ሊቀ መንበር በመሆን ከ20 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ የአክስዮን ማኅበርን ባሕል እንዲሆን ሠርተዋል፡፡ የትራንስፖርት ኩባንያ እንዲቋቋም አስተባብረዋል፡፡ ፊታውራሪ ዐመዴ የእምነትና ዘር ገደብ የማይዛቸው፣ ሀገራቸው ሰላምና የበለጸገች ሆና የማየት ሕልም የነበራቸው፣ በሽምግልናቸው የማያፍሩ፣ እውነትን በብርቱ የሚደፍሩ ሁለገብ አባት ነበሩ፡፡ ያረፉት በ2001ዓም በሚያዝያ ወር ነው፡፡