የ2006 ተሸላሚዎች ዝርዝር

 

በቅርስ፣ ባህልና ቱሪዝም ዘርፍ

ሼክ አብዱላሂ ሸሪፍ

የሐረር ሸሪፍ ሙዝየም መሥራችና ባለቤት የተማሩት የአካውንቲንግ ሞያ የሠሩት በጭላሎ እርሻ ልማት ቢሆንም የሀገራችን ታሪክና ቅርስ ጉዳይ የሚቆጫቸው ሰው ናቸው፡፡ ከ23 ዓመት በፊት የሐረርን ታሪክ፣ ቅርስ፣ የወግ ዕቃዎች፣ በቁፋሮ የተገኙ ታሪካዊ መረጃዎች፣ መጻሕ ፍትና ሌሎችንም በቤታቸው ውስጥ ማሰባሰብ ጀመሩ፡፡ ሙስሊም ክርስቲያኑ የሚያምናቸውና የሚያከብራቸው አብዱላሂ ሸሪፍ ሕዝቡ ሥራቸውን ተመልክቶ ያገኛቸውንና በእጁ የሚገኙትን መረጃዎችና ቅርሶች ይሰጣቸውነበር፡፡ ለ17 ዓመታት ቤታቸውን ሙዚየም አድርገው ሲያሰባስቡና ሲያሳዩ የነበሩት አብዱላሂ ሸሪፍ ለሥራው ዋናው የገቢ ምንጫቸውም የራሳቸው ገቢ ነበር፡፡

ለ17 ዓመታት ሲሠሩበት የነበረው ቤታቸው ‹‹በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግለሰብ የቅርስ ስብስብ›› ተብሎየተመዘገበ ሲሆን በ1990/91 ዓም ወደ ሌላ ቦታ ተዛወረ፡፡ የሼክ አብዱላሂ ሸሪፍ ሙዝየም የሐረር ገዥ የነበሩት ራስ ተፈሪ ወደ ነበሩበት ቤት በ1990/91 ዓም የተዛወረ ሲሆን ዛሬ ይህ ሙዝየም ‹‹ሸሪፍ የሐረር ከተማ ሙዝየም›› ተብሎ ተሰይሟል፡፡ በዚህ ሙዝየም ውስጥ ከ1200 በላይ ጥንታውያን መጻሕፍት፣ ከ400 ሰዓታት በላይ የሚወስዱ ጥንታውያን የድምጽ መረጃዎች፣ ጥንታውያን ሳንቲሞችን፣ ከመካከለኛው ዘመን ጀምረው የነበሩ የጦር መሣርያዎችን፣ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ ፎቶዎችን፣ የሐረርን የንግድ ግንኙነት የሚያሳዩ ሳንቲሞችን፣ መዛግብትን፣ የወግ ዕቃዎችን ሰብስበዋል፡፡

እነዚህ ቅርሶች በዋናነት የሐረሪ፣ የአርጎባ፣ የአማራ፣ የኦሮሞና የጉራጌ ቅርሶች ናቸው፡፡ በሐረርና አካባቢው በተደረጉ ቁፋሮዎች የተገኙ መስቀሎች፣ የአንገት ማተቦች፣ የነገሥታት ማኅተሞች በአብዱላሂ ሸሪፍ ሙዝየም ውስጥ አሉ፡፡ ሼክ አብዱላሂ ሸሪፍ በተለይም ጥንታውያን የብራና መጻሕፍትን፣ መዛግብትን፣ ፎቶዎችንና ሥዕሎችን ወደ ዲጂታል ቅጅ የመገልበጡን ሥራም እያከናወኑት ነው፡፡ ‹‹ጎብኚዎችና ተመራማሪዎች ቅርሶቹንና መዛግብቱን ሳይጎዱ የሚፈልጉትን መረጃ በቀላሉ ያገኛሉ፡፡ ከዚህም በላይ ዋናው ቅጅ ቢጠፋ በውስጡ ያለውን ነገር ለታሪክ ማቆየት ይቻላል፡፡ ቢዘረፍም ቅጅውን በማስረጃነት በመያዝ ለመከራከርም ይመቻል›› ይላሉ- ቅርሱን በማሰባሰብ፣ በመመዝገብና በመጠበቁ ሥራ የሼክ አብዱላሂ ቤተሰብ በነቂስ ነው የሚሳተፈው፡ለዚያውም ከመሥዋዕትነት ጋር፡፡ ‹‹ሦስቱ ልጆቼና ባለቤቴ እነዚህን ዘመን የተጫናቸውን መዛግብት ሲያገላብጡ የአስም ሕመምተኞች ሆነዋል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ሥራውን አላቋረጥንም›› ይላሉ በኩራት፡፡

Tesfaye 

በኪነ-ጥበብ ዘርፍ

ታላቁ የጥበባት ባለሃብት ተስፋዬ ሣሕሉ

ሰኔ 12 ቀን 1916 ዓም ባሌ ውስጥ ከዱ በሚባል ቦታ ተወለዱ፡፡ የትምህርት ዕድል ያገኙት ወላጆቻቸው ወደ ሐረር ከተዛወሩ በኋላ ነው፡፡ በአሥራ አራት ዓመታቸው አባታቸው አቶ መንበረ ወርቅ ለሚባ ሰው አደራ ሰጥተዋቸው ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡ አሳዳጊያቸውና ቤተሰቦቻቸው በጣልያን ጦርነት በማለቃቸው መጀመሪያ ጫማ በመጥረግ በኋላም በሆስፒታሎች አካባቢ በማገልገል ራሳቸውን ለመደገፍ ሞከሩ፡፡ ከዚያም ደግሞ በእቴጌ ሆቴል(ጣይቱ ሆቴል) ተቀጥረው ሠርተዋል፡፡ እዚሁ ሆቴል ሲሠሩ መጀመሪያ ክራርና ማሲንቆ ቀጥለውም ፒያኖ መጨዋት ጀመሩ፡፡ ከጣልያኖች ጋ በተፈጠረ አለመግባባት ከአዲስ አበባ ሐረር ተላኩ፡፡ እዚያ እያሉ ጣልያን ከኢትዮጵያ ተባረረ፡፡ በሐረርም የራስ ሆቴል የምግብ ቤት ኃላፊ ሆነው ተቀጠሩ፡፡ በ1934 ዓም በጦርነት ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ልጆች ይሰብሰቡ ሲባል አባባ ተስፋዬ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ በዚሁ ዓመትም ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ልጆች የሚማሩበት ትምህር ቤት ገብተው መማር ጀመሩ፡፡ 

በ1937 ዓም የማዘጋጃ ቴአትር ቤት ሰዎችን ሲሰበስብ አባባ ተስፋዬም ገብተው ለ11 ወራት ተማሩ፡፡ ከትምህርት በኋላ እነ ደጃዝማች ተክለ ሐዋርያት ቴአትር ማሠራት የጀመሩበት ጊዜ ነበርና አባባ ተስፋዬም ወደ መድረክ ብቅ አሉ፡፡ የመጀመሪያውን ቴአትርም የተጫወቱት ሴት ገጸ ባሕርይን ወክለው ነበር፡፡ በ1948 በብሔራዊ ቴአትር ተቀጠሩ፡፡ በዚያም ከሰባ በሚበልጡ ቴአትሮች ላይ ተጫውተዋል፡፡ 

አባባ ተስፋዬ ከመድረክም በተጨማሪ በቴሌቭዥን የምትሐት ትርዒቶችን ያቀርቡ ነበር፡፡ በዚህ የቴሌቭዥን ትርዒት በሰዎች ዘንድ አድናቆትን አላተረፉበትም፡፡ ያስደነቃቸው በልጆች ፕሮግራም ‹፣የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች›› እያሉ ለ42 ዓመታት ያቀርቧቸው የነበሩ ልጆችን የሚያንጹ ታሪኮቻቸው ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በ1957 ዓም ሲቋቋም ኅዳር 1 ቀን ‹‹ጤና ይስጥልኝ ልጆች፣ የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች›› ብለው በቴሌቭዥን ቀረቡ፡፡

አባባ ተስፋዬ በኪነ ጥበብ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ከኢትዮጵያ የኪነ ጥበባትና መገናኛ ብዙኃን ሽልማት ድርጅት በ1991 ዓም የሕይወት ዘመን ሽልማት አግኝተዋል፡፡ አባባ ተስፋዬ ሕጻናትን በሥነ ምግባር ኮትኩቶ በማሳደግ ታሪክ የማይዘነጋው ሥራ የሠሩ አባት ናቸው፡፡

በሰብዓዊ አገልግሎት ዘርፍ

ዶክተር በላይ አበጋዝ

ታዋቂ ኢትዮጵያዊ የልብ ሐኪም ዶክተር በላይ አበጋዝ የተወለዱት ህዳር 13 ቀን 1937 ዓ.ም በደሴ ከተማ ሲሆን በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ያጠኑት ደግሞ ሕክምና ነው፡፡ በኋላም በሕጻናት ልብ ህክምና ስፔሻላይዝድ አደረጉ፡፡ ዶክተር በላይ ከ1973 ዓም ጀምረው ላለፉት 30 ዓመታት በሕጻናት ሕክምናና በሕጻናት ካርዲዮሎጂስትነት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር አገልግለዋል፡፡ 

ፔዲያትሪክስን በማስተማር፣ ስለ ሞያውም ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማሳተም ይታወቃሉ፡፡ከ1981 ዓም ጀምረው የአሜሪካ ፔዲያትሪክስ አካዳሚ አባል ሲሆኑ፣ በInternational Society of Hypertension in Blacks, The Pan African Society of Cardiology, The National Drug Advisory Board of Ethiopia አባል ሲሆኑ በEthiopian Medical Journal በአባልነት፣ በረዳት ዋና ጸሐፊነትና በሊቀ መንበርነት አገልግለዋል፡፡ 

ዶክተር በላይ አበጋዝ የማይረዱትና የማያግዙት የዓለም ክፍል የለም ለማለት ያስችላል፡፡ የHealing the Children USA, Save a Child's Heart ISREAL and Chain of Hope UK ተባባሪ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ላየንስ ክለብ አባልና ዋና አራማጅ ናቸው፡፡

ዶክተር በላይ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ድርጅት መሥራችና የቦርድ ሊቀ መንበር ሲሆኑ የልብ ሕመም ያለባቸው ሕጻናት ውጭ አገር ሄደው ለመታከም የሚያስችል ዐቅም ስለሌላቸው የሚያጋጥማቸውን ጉዳት ለመቀነስ በመላው ዓለም ዞረው የመሠረቱት ከሀገራችን ችግር ፈቺ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ የህጻናት የልብ ህክምና ሆስፒታልን ለመክፈት ያላሰለሰ ጥረት አድርገው ራዕያቸውን አሳክተዋል፡፡ የብሩክ የሕክምና አገልግሎቶች ድርጅት ባለቤት የሆኑት ዶክተር በላይ በአሁኑ ጊዜ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ በማድረግ በሕፃናት ልብ ህክምና የማማከር አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

 

በንግድ፣ ኢንዱስትሪ፣ ግብርናና ስራ-ፈጠራ ዘርፍ

ቤተልሔም ጥላሁን

ወ/ሮ ቤተልሔም ጥላሁን ሶል ሪብልስ የተሰኘው በአፍሪካ ታዋቂ ከሆኑት ጫማ አምራቾች አንዱን የመሠረቱና የሚመሩ ሰው ናቸው፡፡ ድርጅቱን የመሠረቱት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2005 ዓም ሲሆን ዋና ተግባሩም ኢትዮጵያ ውስጥ በባሕላዊ መንገድ ጥቅም ላይ ይውል ይነበረውን በርባሶ ጫማ በዘመናዊ መንገድ አምርቶ ለዓለም ገበያ ማዋል ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዘነበ ወርቅ አካባቢ ተወልደው ያደጉት ወ/ሮቤተልሔም ጥላሁን በአካባቢያቸው ያሉ ሰዎች በድህነት ምክንያት ብዙዎቹ ሥራ አጦች መሆናቸውን፤ ነገር ግን ማንም ያልተጠቀመበት ክህሎት ያላቸው መሆኑን በማስተዋል የእነዚህን ወገኖች አቅም ወደ ምርትና ገበያ ለመለወጥ ተነሡ፡፡ በዚህም መሠረት እኤአ በ2004 ዓም ከባለቤታቸውና ከቤተሰቦቻቸው ባገኙት የመነሻ ገንዘብ በመጠቀም በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ከሚገኙ ታዋቂ የጫማ አምራቾች አንዱ የሆነውን ሶል ሪብልስ የተሠኘውን ኩባንያ መሠረቱ፡፡

በባሕላዊ መንገድ ይመረቱ የነበረውን የበርባሶን የአመራረት መንገድ በዘመናዊ መልክ በማምጣት ለአካባቢ ብክለት አስተዋጽዖ የማያደርግ፣ ካርቦን ዜሮ የሆነ ጫማ ለማምረት ችለዋል፡፡ በዚህ ሥራም ከ100 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን በሥራ ላይ ከማሠማራታቸውም በላይ በሠላሳ የዓለም ሀገሮች ምርታቸውን በማከፋፈል የሀገሪቱን ስም እያስጠሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሥራቸውም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ተቀብለዋል፡፡ በ2011 መጀመሪያ ላይ የዓለም የኢኮኖሚክ ፎረም ‹‹አዳጊዋ የዓለም መሪ›› ተብለው የተመረጡ ሲሆን በሰኔ 2011 ደግሞ ‹‹እጅግ የተዋጣላቸው የንግድ ሰው›› የሚለውን ሽልማት በአፍሪካ ቢዝነስ መጋዚን አግኝተዋል፡፡ በጥቅምት 2011 ደግሞ በዓለም የኢንተርፕርነሮች ሳምንት ‹‹እጅግ የተወደዱ ኢንተርፕርነር›› ተብለው ተሸልመዋል፡፡

 በማህበራዊ አገልግሎት፣ ሃገራዊ ሰላምና ዕርቅ ዘርፍ

ብጹዕ አቡነ ዮናስ

ብጹዕ አቡነ ዮናስ የአፋር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ ወደ አፋር አካባቢ የመጡት በ1972 ዓም ነው፡፡ የሁሉም አባት በመባል በአካባቢው ሕዝብ ዘንድ የሚጠሩት አቡነ ዮናስ አያሌ የአፋር ልጆችን ፊደል ያስቆጠሩና ለከፍተኛ ማዕረግም ያደረሱ ናቸው፡፡ በተለይም በአፋር አካባቢ ያለው የመጠጥ ውኃ ችግር እንዲቀረፍ ገጠር ወርደው በማስተማር ሕዝቦ ችግሩን ራሱ እንዲቀርፍ አነሣስተዋል፡፡ ለአካባቢው አረጋውያን መኖሪያ 5227 ካሬ ሜትር በሆነ ቦታ ላይ እየሠሩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ 50 አረጋውያን በቦታው ይረዳሉ፡፡ ይህንን የአረጋውያን መርጃ ፕሮጀክት ለመደገፍም 7 ሄክታር መሬት ከመንግሥት ተቀብለው ከጃፓን ኤምባሲ ጋር በመሆን የአካባቢውን ሕዝብ አስተባብረው እያለሙ ናቸው፡፡

ቁጥራቸው የማይታወቅ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆች በራሳቸው ወጭ የሚያስተምሩ ሲሆን ከንቱ ውዳሴ እንዳያመጣባቸው ሲሉ ቁጥሩን አይናገሩም፡፡ በአዋሽ አርባ አካባቢ በረሃማነትን ለመቀነስ እንዲቻል በራሳቸው በመሥራትና የአካባቢውን ሕዝብ በማስተባበር አያሌ ዛፎችን በማስተከል አካባቢውን ቀይረውታል፡፡ ይህንን ዛፍ ለመከባከብና ተሞክሮውንም ወደ ሌላ ለማስተላለፍ አካፋና ዶማቸውን ይዘው ዛሬም እንደተሰለፉ ናቸው፡፡

 

በጥናትና ምርምር ዘርፍ

አምባሳደር ዘውዴ ረታ

ጋዜጠኛ ዲፕሎማትና ደራሲ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ነሐሴ 7 ቀን 1927 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተወለዱ፡፡ ቀድሞ ደጃዝማች ገብረ ማርያም ይባል በነበረውና ኋላ ‹‹ሊሴ ገብረ ማርያም›› ተብሎ በተሰየመው የፈረንሣይ ትምህርት ቤት የመጀመ ሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ከ1948 ዓ.ም እስከ 1952 ዓ.ም በፓሪስ የጋዜጠኝነት ሞያ ተምረው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ የሊሴ ገብረማርያምን ትምህርት ለጊዜው አቁመው እያሉ በ1945 ዓ.ም የራዲዮ ዜና አንባቢ ሆነው ሥራ ጀመሩ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አምባሳደር ዘውዴ ረታ በጋዜጠኝነት በዲፕሎማትነትና በመጨረሻም በደራሲነት በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ 

ከ1945 ዓ.ም እስከ 1967 ዓ.ም በጋዜጠኝነት ሙያ በጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት የቤተ መንግሥት ዜና ጋዜጠኛና በራዲዮ ዜና አቅራቢ፣ የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣና የመነን መጽሔት ዲሬክተር፣ የኢትዮጵያ ራዲዮ የብሔራዊ ፕሮግራም ዲሬክተር፣ የኢትዮጵያ ወሬ ምንጭ ዋና ዲሬክተር ሆነው አገራቸውን አገልግለዋል፡፡ በአስተዳደሩ ዘርፍም የማስታወቂያ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የፓን አፍሪካ ኒውስ ኤጀንሲ ማኅበር ፕሬዘዳንት ሆነው ሠርተዋል፡፡

በዲፕሎማሲው መስክ በፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሚኒስትር ካውንስለር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር እና በሮምና በቱኒዝያ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ለሃያ ሁለትዓመታት ካገለገሉ በኋላ በደርግ ዘመነ መንግሥት በአውሮፓ በቆዩባቸው አሥራ ሦስት ዓመታት በሮም የኢንተርናሽናል ድርጅት /IFAD/ ውስጥ በፕሮቶኮልና የመንግሥታት ግንኙነት ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ 

አምባሳደር ዘውዴ ጋዜጠኛና ዲፕሎማት ብቻ ሳይሆኑ ደራሲም ናቸው፡፡ በ1945 ዓ.ም እና 1946 ዓ.ም ‹‹እኔና ክፋቴ›› እና ‹‹የገዛ ሥራዬ›› የተሰኙ አስቂኝ ቲያትሮችን ጨምሮ አራት ቲያትሮችን ጽፈዋል፡፡ ‹‹በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሠት የኤርትራ ጉዳይ››፣ ‹‹ተፈሪ መኮንን ታላቁ የሥልጣን ጉዞ›› እና ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት›› የተሰኙ በዳጎስ ዳጎስ ያሉ የታሪክ መጻሕፍትን ለአንባብያን አበርክተዋል፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የምኒልክ የመኮንን ደረጃና የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ አዛዥ መኮንን ኒሻን እንዲሁም ከአፍሪካ ከእስያና ከአውሮፓ በድምሩ ከሃያ ሁለት አገሮች የታላቅ መኮንን ደረጃ ኒሻኖች ተሸልመዋል፡፡

 

መንግስታዊ ሃላፊነትን በብቃት በመወጣት ዘርፍ

አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ

አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ ለሃምሳ ሁለት ዓመታት አገራቸውን በዲፕሎማሲ መስክ ያገለገሉ አንጋፋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዓመታት አገራችንን ወክለው በተባበሩት መንግሥታት፣ በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በአፍሪካ ህብረት በሠሩባቸው ጊዜያት በዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት፣ በፖለቲካዊ ጉዳዮች፣ በሰብዓዊ መብት፣ በስደተኞች፣ ትጥቅ በማስፈታት፣ በጸረኮሎኒያሊዝምና በመሳሰሉት ሰፊ እውቀትና የሥራ ልምድ አላቸው፡፡ 

እ.አ.አ. በ1962 ዓ.ም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የዲፕሎማትነት ሥራቸውን የጀመሩት በተባበሩት መንግሥታት መምሪያ ውስጥ ሦስተኛ ጸሐፊ ሆነው ነበር፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ ዕድገት አግኝተው በሁለተኛ ጸሐፊ ማዕረግ ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽ/ቤት እንዲሠሩ ተመደቡ፡፡ በዚህ ኃላፊነት ለአምስት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ እ.አ.አ. በ1970 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በቅድሚያ በአፍሪካ መምሪያ ቀጥሎም በዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ገለልተኛ አገራት መምሪያ ውስጥ በፖለቲካ ኦፊሰርነት ሠርተዋል፡፡ ከዚያም ወደ አንደኛ ጸሐፊነት አድገው የተባበሩት መንግሥታትና በገለልተኛ አገራት መምሪያ ተጠባባቂ የመምሪያ ኃላፊ ሆነው ተመድበዋል፡ በመቀጠልም ጄኔቭ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት ውስጥ የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው እንዲሠሩ ተመድበዋል፡፡ 

አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ በመጋቢት 1982 ዓ.ም ስዊዘርላንድ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እንዲሠሩ ተሹመዋል፡፡ ከዚህ ጋር በማያያዝ ተቀማጭነታቸው በስዊዘርላንድ ሆኖ በኦስትሪያ ፌደራል ሪፐብሊክና በቪየና በሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ በተመሳሳይ ኃላፊነት እንዲሠሩ ተደራራቢ ሹመት ተሰጥቷቸው አገልግለዋል፡፡ ከመጋቢት 1984 ዓ.ም አንስቶ በካናዳና በሜክሲኮ በኋላም በእስራኤል የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እስከ ነሐሴ 1987 ዓ.ም ድረስ ሠርተዋል፡፡ በዚሁ ወር ወደ አገር ቤት ተመልሰው በመጀመሪያው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እንዲሠሩ ተሹመዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ በግብጽ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ከአራት ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ አዲስ አባባ ተመልሰው ለሁለተኛ ጊዜ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የአፍሪካ ጉዳዮች ጄነራል ዳይሬክተር ሆነው እንዲሠሩ ተሹመዋል፡፡ እ.አ.አ. በ2006 ዓ.ም በኦስትሪያ ፌደራል ሪፐብሊክና በቪየና በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እንዲሠሩ በድጋሚ ተሹመዋል፡፡ ከመስከረም ወር 2002 ዓ.ም እስካሁን ድረስ በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው አገራቸውን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ 

አምባሳደር ቆንጂት በእነዚህ አምስት አስርት ዓመታት ውስጥ በዲፕሎማሲው መስከ ባከናወኑት ተግባር በጠንካራነታቸው የሚታወቁ፣ አገራችንና የሥራ ባልደረቦቻቸው የሚኮሩባቸው አምባሳደር ናቸው፡፡