የ2005 ተሸላሚዎች ዝርዝር

 

በትምህርት ዘርፍ

ንቡረ ዕድ ተፈራ መልሴ

የርእሰ አድባራት አዲስ ዓለም ማርያም አስተዳዳሪ ናቸው፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በትምህርት ያላደረሱት መስክ የለም፤ በሲመትም የታላቋ ደብር አለቃ ሆነዋል፡፡ ይህ እልቅናቸው እንደ ሌሎቹ ቤት ልሥራ፤ ዘር ልዝራ አላሰኛቸውም፡፡ ነገር ግን ሀገራዊ ጉዳይ ያሳስቸው ነበር፡፡ እርሳቸው አረጋዊ ናቸው፤ በእርጅና ጎንበስ ብለው ድካምን የሚጋፉት፤ እርሳቸው በዕድሜ ጣርያ ላይ ያሉ ናቸው፤ ዐርፈው መቀመጥ የሚያስፈ ልጋቸው፤ ግን እንዲህ አላደረጉም፡፡ በዚህ የእርጅና ዕድሜያቸው በመላው ዓለም እየዞሩ፣ እየለመኑና እያባበሉ ኢትዮጵያዊ ዕውቀት የሚገኝባቸው፣ ነገር ግን እንደ ዋልያና ቀይ ቀበሮ በመጥፋት ላይ ያሉት የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዲጠበቁ፣ ተሻሽለውም እንዲቀጥሉ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማሰባሰብ ተግተዋል፤ ድካም ሳያግዳቸው የሰው ፊት እያዩ ለአብነት ትምህርት ቤቶች የሚሆን ገንዘብና ቁሳቁስ ሰብስበዋል፡፡ 

ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመሆን በወጠኑት በዚህ አገልግሎት ዛሬ ከመጥፋት ድነው፣ ከመድከም በርትተው ታሪካዊውን፣ ሃይማኖታዊውንና ሀገራዊውን ዕውቀት የሚያካሂዱ አያሌ የአብነት ትምህርት ቤቶችን አፍርተዋል፡፡ ያሉትን ከመጠበቅም በላይ አዳዲሶች በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ እንዲከፈቱ አድርገዋል፡፡ አረጋዊው ንቡረ ዕድ ገብረ ሕይወት መልሴ!

 

በጋዜጠኝነትና ሚዲያ ዘርፍ

ጋዜጠኛ መአዛ ብሩ

በመረዋ ድምጽ፣ ልብን ሰርሥሮ በሚገባ፣ ቤተኛ በሚያደርግ የቃለ መጠይቅ ጥበብ እንደ መልካም ወገኛ በማጫወት የተካነች ናት፡፡ ለጋዜጠኝነት ሞያ ባላት ፍቅር ኢትዮጵያዊ መልክ ያላቸውን፣ ታሪክና ባህልን የሚያስታውሱንን ታላላቅ ሰዎቻችንን እንድናውቅ የሚያደርጉንን ፕሮግራሞች የሚያቅፍ የሬዲዮ ጣቢያ በመመ ሥረትና በመምራት፣ ታላላቅ ሰዎቻችንን ሞት ሳይቀድመን በፊት ቅርስ ሆነው እንዲቀሩ፣ የማይታወቁ ጀግኖቻችን ለአደባባይ በቅተው እንዲታወቁ በማድረግ፤ አንድ የተለየ ጣዕምና ሚና፣ አንድ የሚደመጥና የሚናፈቅ፣ አንድ ልዩ ቀለምና ጠባይ ያለው የሬዲዮ መሥመር ሸገር ሬዲዮን በመዘርጋት የተዋጣለት ተግባር እያከናወነች ትገኛለች፡፡ ዕወቁኝ ዕወቁኝ አትልም፣ ስለ ራሷም ማውራት አትወድም፣ ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ እንዲል ግን ሥራዋ ማንነቷን ገልጦላታል፡፡

ዛሬ የሰላምታ ያህል ከብዙዎች የሚደመጠውን ‹ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር› የሚለውን ጣፋጭ ሐረግ ገና የሬዲዮ ጣቢያ ሳይኖራትና የቅዳሜ ጨዋታን በኤፍ ኤም 97.1 ላይ ከሌሎች አጋሮቿ ጋር ስታዘጋጅ ጀምራ መርሕ አድርጋ ይዛዋለች፡፡ መዓዛ ብሩ!

በሰብዓዊ አገልግሎት ዘርፍ

የሜቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ መስራች

ቢኒያም በለጠ

የ35 ዓመት ወጣት ነው፡፡ አያቱ በጎንደር ከተማ የታወቁ ነበሩ፡፡ ችግረኞችን በመርዳትና ሰው ለሌላቸው ሰዎች መጠጊያ በመሆን ነበር የሚታወቁት፡፡ እንዲያውም የተቸገረ ሰው ላመጣላቸው ሰው ወሮታውን በእህል ይከፍሉ እንደነበረ የከተማው ሰዎች ዛሬም ያስታውሷቸዋል፡፡ አባቱም በዚያው መንገድ ተጓዙና ሰው መርዳት ሆነ ነገር ዓለማቸው፡፡ በወቅቱ የሼል ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አባቱ አቶ በለጠ ደመወዛቸው 4000 ብር ነበር፡፡ በቤት ውስጥ ግን ልጆቻቸው ሽሮ እንኳን አጥተው ጦም የሚያድሩበት ጊዜ ነበር፡፡ጠጥተውበት አይደለም፣ ቁማር ተጫዉተዉ ተበልተውም አልነበረም፡፡ ለችግረኞች የሚራሩ በመሆናቸው ለድኾች አከፋፍለው ስለሚጨርሱት እንጂ፡፡ መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ ያፈራል ነውና፤ ይህንኑ በጎ ነገር ልጃቸውም ወረሰው፡፡ ለታክሲ የተሰጠውን ገንዘብ በእግሩና በአውቶቡስ እየተጓዘ በመቆጠብ ችግረኛ ተማሪዎችን ይረዳበት ነበር፡፡ እንዲህ እየኖረና እየተማረ አድጎ አሥራ ሁለተኛ ክፍል አራት ነጥብ አመጣ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ገብቶ ሕግ ተማረ፡፡ ከዚያም ተመርቆ ጥቂት ጊዜ ሠራና አሜሪካ ገባ፡፡ እዚያም ከቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ የማስትሬት ዲግሪውን ሠራ፡፡ እዚያ አረጋውያንን በሚንከባከብ ድርጅት ውስጥ ሲሠራ የሀገሩን አረጋውያን ነበር በልቡ የሚያስበው፡፡ እንዲያም ብሎ እዚያ እየሠራ ገንዘብ በመላክ እዚህ የሠፈሩን ድኾች ይረዳ ነበር፡፡ እንዲህ እንዳደገው ዓለም የሚንከባከባቸውና ርግማናቸውን ሳይሆን ምርቃታቸውን የሚያተርፍ ተቋም በሀገሬ መቼ ነው የሚኖረው? እያለም ያስብ ነበር፡፡ እዚያ ማዶ ሆኖ የሚልከው ገንዘብ እዚህ በሚገባው ቦታ እየዋለና የሚፈለገውን ውጤት እያመጣ አለመሆኑን አየና ነገር ዓለሙን ሁሉ ጥሎ ሀገሩ ገባ፡፡ በቤተሰቦቹ ቤት ይህንን ክብር ያለው ግን ቆራጥነትና ትዕግሥት፣ ትጋትና ቻይነት የሚጠይቅ አገልግሎት ሲጀምረው፤ ቤተሰቦቹ፣ ጓደኞቹና ወዳጆቹ ሁሉ ‹አበድክ› ብለውታል፡፡ እርሱ ግን አለማበዱን በተግባር ለማሳየት ተጋ፡፡ ቀስ በቀስም ተቃዋሚዎቹን ሁሉ ተባባሪ አደረጋቸውና ‹መቄዶንያ የአረጋውያን መርጃ ድርጅትን›_መሠረተ፡፡ ዛሬ በዚህ ድርጅት 170 አረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን ይረዳሉ፡፡ እርሱም መኖርያው ከአረጋውያኑ ጋር ነው፡፡ የበሉትን ይበላል፤ የጠጡትን ይጠጣል፡፡ አቶ ብንያም በለጠ!

   

በኢኮኖሚ መስክ አዲስ መንገድ በማሳየት

 የምርት ገበያ መስራች

ዶክተር እሌኒ ገብረመድኅን

የአፍሪካ የምግብ ችግር ከምርት ብቻ ሳይሆን ከምርቱ ገበያ ጋር የተያያዘ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ በዚህም የተነሣ ከሰሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገሮች ላይ ሠርተዋል፤ ተመራምረዋል፡፡ በዓለም ባንክ፣ ዋሽንግተን በሚገኘው ዓለም ዐቀፍ የምግብ ፖሊሲ ጥናት ማዕከል፣ እና በተባበሩት መንግሥታትም በከፍተኛ ኃላፊነት ሠርተዋል፡፡ በኢኮኖሚክስ ዲግሪያቸውን ከኮርኔል ዩኒቨርሲቲ፣ ማስትሬታቸውን ከሚችጋን ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፤ በአፕላይድ ኢኮኖሚክስ ደግሞ ፒ ኤች ዲያቸውን ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ወስደዋል፡፡ ለምግብ እህል እጥረት አንዱ ችግር የገበያው ሁኔታ ነው የሚከለውን የጥናት ውጤታቸውን እውን ይዘው ከነ መፍትሔው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2004 ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ሃሳባቸውን ወደ ተቋም በመለወጥም በኢትዮጵያ የምርት ገበያ እንዲመሠረት ዋነኛዋ ሐሳብ አፍላቂና አንቀሳቃሽ ኃይል ሆነው ሠሩ፡፡ በዚህም ምርምርንና ጥናትን በጥራዞች ላይ ከማዋል ባሻገር ለሀገር ችግር መፍትሔ አድርጎ መጠቀም እንደሚገባ አሳዩ፡፡ ዛሬም ናይሮቢ ላይ ከመሠረቱት ቢሮ እየተነሡ በአፍሪካ ይህንኑ ሐሳባቸውን ለማካፈልና አፍሪካን ከምግብ እጥረት ለማላቀቅ በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ዶ/ር ዕሌኒ ገብረ መድኅን!

የወጣቱን የንባብ ባህል በማሳደግ

ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ

ደራሲ ነው፡፡ ሰባት ያህል መጻሕፍትን አቅርቦልናል፡፡ የተወለደው ወልቂጤ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሚከታተልበት ጊዜ ‹ተስፋ› ብሎ በሰየማት አነስተኛ የመጻሕፍት መደብሩ ለከተማዋ ነዋሪዎች እጅግ አነስተኛ በሆነ ዋጋ እያከራየ የንባብ ባሕል እንዲዳብር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ እንደ ተከራዮቹ ሞያና የትምህርት ደረጃ ስለ መጻሕፍቱ አጭር ማብራርያ እየሰጠ፤አንብበው ሲመልሱም ስለ መጻሕፍቱ አስተያየት እየተቀበለ ያበረታታ ነበር፡፡ በወልቂጤ ከተማ ውጤታማነትን ለማበረታታት በራሱ ተነሣሽነት በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ሽልማቶችን ይሸልማል፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሲሆን በዚህ የሥራ ድርሻው አዳዲስ ሐሳቦችን በማመንጨትና በመተግበር ደራስያን እንዲጠቀሙ ድርሰትም እንድታብብ እያደረገ ነው፡፡ በገንዘብ እጥረት ምክንያት የአእምሮ ሥራቸውን ማሳተም ላልቻሉ ደራስያን በተዘዋዋሪ ገንዘብ ድርሰቶቻቸውን የማሳተሙን ሐሳብ አቅርቦ ከሌሎች ጋር ሆኖ እንዲተገበር አድርጓል፡: ከኢትዮጵያ ጡረተኞች/አዛውንቶች ጋር በመተባበር መድረኮችን አዘጋጅቶ ወጣቶችና አረጋውያን ተገናኝተው ልምድ እንዲለዋወጡ አድርጓል፤ በወር አንድ ጊዜ በብሔራዊ ቴአትር የሕጻናት ዝግጅት በሕጻናት እንቀዲርብ በማድረግ ፣ የንባብ ባህል በሕጻናት ላይ እንዲዳብር የሚችለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ እንዳለ ጌታ ከበደ!